የታወቀ ነው፤ የተለመደ! በየተረቶቻችንና ሥነ-ቃሎቻችን አንበሳ መሪ
ተዋናይ ነው፤ ያለእሱ መድረኩ አይደምቅም፤ ምልልሱ አይሞቅም፤ በተቃራኒው ደግሞ አህያን ረዳት ተዋናይ አድርገን ልንቆጥረው
እንችላለን፤ ቢኖር ያገለግላል ባይኖር ደግሞ ብዙም አያጐድል ተብሎ ችላ የሚባል፡፡
ይኼ መጣጥፍ በሕይወት መድረክ ላይ ሁለቱንም ሆነን የመተወን
እድል ስለገጠመን ሰዎች ለመተረክ የሚሞክር ነው፤ አንበሳ ሆነን ወይም ተብለን በህይወት ሳለን ስለተፈራን ሞተን ስንገኝ ደግሞ
ሐውልት ስለቆመልን ሰዎች፤ አህያ ሆነን ወይም ተብለን በህይወት ሳለን በጫንቃችን ላይ ውርደት በጭንቅላታችን ላይ ስቅየት
ስለተፈራረቀብን፤ ሞተን ስንገኝ ደግሞ ለማንም ጥንብ ጐታች ስለምንሰጥ ሰዎች የሚተርክ…
እውነት ነው አንበሳ መሆን ደስ ይላል፤ ‹ሞኣ አንበሳ
ዘእምነገደ ይሁዳ…› መባል ደስ ይላል፤ አንበሳ ምሳሌነቱ ከድሮ ጀምሮ ለተወደደ እና ለተከበረ ነገር ነው፤ ኢየሱስም ከይሁዳ
ዘር ነው ብለን ዘር ማንዘሩን እንቆጥራለን፤ ከአንበሳው ወገን የሚመደብ! እናም የፊተኞቹ ነገሥታት ‹አንበሳነት ከጥንት ጀምሮ
በደማችን የተዋኸደ ነው› ለማለት፤ የተቀደሰውን ነገር ‹ያደግንበት ነው› ለማለት፤ ‹ሞኣ አንበሳ…› ይላሉ፤ መጽሐፍ ቅዱስ
በአንድ በኩል አንበሳን እንዲህ ለተባረከ ነገር አሳልፎ ሲሰጠው፤ በሌላ ምዕራፍ ላይ ደግሞ አንበሳን በዲያብሎስ ይመስለዋል፤
በነጣቂ፣ በአስጨናቂ፣ በእንቅልፍና በእረፍት ሰራቂ!
እናም እንዲህ እላለሁ፤ የሀገራችንና የአሕጉራችን ቀደምትና
የአሁን መሪዎች ‹አንበሳ›ነን ብለው ራሳቸውን ሲመስሉ የትኛውን ዓይነት አንበሳ ሆነው አግኝተናቸዋል?
…ከቅዱሳት መጽሕፍት ውጪ፤ አንበሳ በየተረቱ ውስጥ ድል
አድራጊ ነው፤ አንድም አውሬ እፊቱ ይቆም ዘንድ አይቻለውም፤ ‹ንጉሥ› ነው፤ ቀጪ እና ተቆጪ የለውም፤ ንዴቱ ዛፎቹን
ያንቀጠቅጣል፤ ተራሮችን ያርዳል፤ እጁ ውስጥ ከገባን ከመዳፉ ፈልቅቆ የሚወስደን ሃይል ማን ነው?... በርግጥ ይህ ሁሉ ሃይል
አንበሳው ስልጣን ላይ እስካለ ነው፤ ስልጣኑ የሚጠናቀቀው ደግሞ የጉብዝና ወራቱና የወራት ዘመኑ ሲያከትም ነው፤ ከዚያ በኋላማ፤
ዝንቦች መጫወቻ ያደርጉታል፡፡