አስናቀ- ‹ተወዳጁ› ሰይጣን
አበበ ባልቻ (አርቲስት) ‹ሰው ለሰው› የተሰኘውን ተከታታይ የቴሌቪዥን
ድራማ ዝነኛ እንዲሆን አድርጐታል ብዬ አምናለሁ፤ ‹ሰው ለሰው› ድራማ
ከፍ ያለቦታ እንዲሰጠው አበበ ባልቻ ትልቅ ሚና ተጫውቷል ብዬም አምናለሁ፤ ረቡዕ በመጣ ቁጥር፤ መጥቶም በመሸ ቁጥር
ሰዎች ማወቅ ከሚያጓጓቸው ነገሮች መካከል አንዱ ‹አስናቀ እንዴት እንደሰነበተ› መረጃ መለዋወጥ ሆኗል!
‹ሰው ለሰው› ውስጥ ያሉ ገጸ-ባህርያትና ድራማውን በመድረስ፣ በማዘጋጀት፣
በመተወንና ሙያዊ ድጋፍ በማድረግ እየተባበሩ ያሉ ሙያተኞች ስማቸውን በልባችን ውስጥ ማስፃፍ ችለዋል፤ በክብር እንግድነት የሚፈለጉባቸው
መድረኮችም ጨምረዋል፤ በአጠቃላይ የ‹ሰው ለሰው›› ሰዎች የብዙዎቻችን ቤተኞች ሆነዋል፡፡ ይኼ መታደል ነው!! ግና ደራሲዎቹ (በተለይ
ሰለሞን ዓለሙና መስፍን ጌታቸው) በየመጽሔቱ ስለዚህ ተከታታይ ድራማ በሚሰጡት ቃለ መጠይቅ ተባብሮ፣ ተከባብሮና የሚያጋጥሙ ችግሮችን
በብልሃት እንዴት እንደሚወጡት ብናነብላቸውም፤ ድራማው ሊጠናቀቅ እየተቃረበ መሆኑንና ከዓመት በላይ እንደማይቆይ የሰጡትን መረጃ
ልብ ብንለውም፤ እንደ ቴሌቪዥን ድራማው ተከታታዮች፤ እኔንና ጓደኞቼን ሲያሳስቡ የቆዩ ሶስት ነጥቦች አሉ፤ እነዚህ ነጥቦች ከወዲሁ
ማረሚያ ካልተበጀላቸው፤ ማቃኛ ካልተደረገባቸው አንዳንድ ተመልካቾችን ድንዛዜ ውስጥ ሊከቱ ይችላሉ የሚል እምነት አለኝ፡፡
‹ሰው ለሰው› ውስጥ ያሉ ገጸ-ባህሪያትን ወክለው በመጫወት ብዙዎቹ የሚደነቁ
ቢሆንም፤ ገጸ ባህርያቱን በመፍጠር በኩል ግን ደራሲዎች ልብ ያላሏቸው ወይም ችላ ብለው የናቋቸው ወይም በማጠቃለያ ክፍሉ ትኩረት
ሰጥተን እንመለስባቸዋለን ብለው እስካሁን በቅጡ ሲዳስሷቸው ያላየናቸው ነጥቦች አሉ፤ እነሱም አንድ በድራማው ውስጥ ሴቶችን ደካማ
አድርጐ መሳል፤ ሁለት፣ ተመልካቹ እንደ አርአያ የሚወስዳቸው ቤተሰቦች አለመኖር፤ ሦስት፣ ‹ሰይጣን› የሆነውን ገጸባህርይ አጀግኖ
አሳዳጅ ፖሊሱን አኮስምኖ የማቅረብ ሁኔታ…