ልጥፎችን በመለያ አጫጭር ልቦለዶች በማሳየት ላይ። ሁሉንም ልጥፎች አሳይ
ልጥፎችን በመለያ አጫጭር ልቦለዶች በማሳየት ላይ። ሁሉንም ልጥፎች አሳይ

ማክሰኞ 3 ሴፕቴምበር 2013

ከጥቁር ሰማይ ስር



ጥዋት ጥዋት፣ ወደ ቢሮ ለመሄድ - መታጠፊያው ጋ ሲደርስ - እተለመደ ቦታዋ ቁጭ ብላ የሚያጉተመትም በሚመስል ድምጿ ያለማቋረጥ ስታወራ ይሰማታል፡፡ የአራት ልጆች እናት የሆነችዋን የኔ ቢጤ፡፡
የእናታቸውን ያህል ባይሆንም ጎስቁለዋል፡፡ እንደ ምጣድ ማሰሻ የቀድሞ ከለሩ ያልታወቀ ከነቴራ ለብሰዋል - ከወገባቸው በላይ፡፡ ከመሃከላቸው አንዳቸውም ቃጭል አንጠልጥለው አልተወለዱም፡፡
. . . በማያውቀው ቋንቋ ታወራቸዋለች፡፡
ልጆቿ አይመልሱላትም፡፡ እርስ በርሳቸው ሲጨዋወቱ በአዲስ አበባ አማርኛ ነው የሚግባቡት፡፡
እንዲህ በከንቱ ጉንጭዋን የምታለፋው በውስጡ ያደረውን ጩዋሂ መንፈስ ላለማዳመጥ ይሆን? ብሎ ያስባል
ጤንነቷን የማይጠራጠር የለም፡፡ አንዳንዶች ፥ ስለ ልጆቿ የወደፊት ዕጣ ፈንታ ማሰላሰል ስታበዛ ይሆን ያተሳሰብ ማዛንዋ የተዛባው? ይላሉ፡፡
ሁልጊዜ ያልተለመደ ነገር ስታደርግ ያጋጥመዋል፡፡ እጇ ላይ የተገኘን ማንኛውም ነገር ለአራት አካፋፍላ ለልጆች ታድላቸዋለች፡፡ ለራሷ የምታደርገው አይኖራትም፡፡ ከሲታ ናት ደግሞ፤ ያለ እህል ውሃ ለመኖር ሙከራ የጀመረች እስኪመስል ድረስ፡፡
ሳንቲም ተወርውሮ እግሯ ስር ያረፈ እንደሆነ ቅጭልጭልታውን ሰምታ እንኳን ቀና አትልም፡፡ ማንንም አይታይም - አገጯን ጉልበቷ ስር ደብቃ ነው፤ ቀኑን ውላ የምታመሸው፤ የምታነጋውም! መንገድ ዳር፡፡

ማክሰኞ 27 ኦገስት 2013

ሲጨልም



ወደ ሰባዎቹ የሚጠጉ የሚመስሉ አንድ አረጋዊ “ልጄ” አሉት አስተናጋጁን፡፡ “የወሰድኩትን መድኃኒት ይዤብህ መጣሁ፣ እባክህን የሰጠኸኝን ወስደህ . . .”
አላስጨርሳቸውም፡፡ ግርግዳው ላይ ወደተለጠፈው ጽሑፍ አመለከታቸው፡፡ ‘የተሸጠ መድኃኒት አይመለስም አረጋዊው’ በለሰለሱ ቃላት መማፀን ያዙ፡፡
“ሰውዬ ዞር በል! ስራ ልስራበት! ለእንቶ ፈንቶ ጉዳይ የማባክነው ጊዜ የለኝም. . .” አለ ቁጣው እየተወለደ፡፡
“ዛሬ በዚህ ሰውዬ እንድጨቀጨቅ ተፈርዶብኛል ልበል?”
“እባክህን ልጄ አሳፋሪ ነገር ደርሶብኝ ነው ዘመድና ዕድር የለለኝ በመሆኑ እንጂ . . . ” አሉ ትሁት በሆነች ፈገግታ ሊያባብሉት እየሞከሩ፡፡
“ቅናሽ ዋጋ ብትከፍለኝም . . .”
“ይሄ ሰውዬ ነካ ያረገዋል ልበል?” አለና ሌሎች መድኃኒት ገዥዎችን ያስተናግድ ገባ፡፡ “ከያዙ አይለቁ” 

ዓርብ 16 ኦገስት 2013

ምጣዱ



ከርቀት  
አንድ ሰባኪ ድምጹን አስጩሆ የመዝጊያ ጸሎት ሲያካሂድ ይሰማታል፡፡
“የዕለት እንጀራችንን ስጠን ዛሬ . . .”
“አሜን” አለች - ፈገግ ብላ፡፡ አልጋዋን ዐየችው - የዕለት እንጀራዋን የምትጋግርበት ምጣዷን፡፡
አሁን የምትኖርበት ክፍል - ነፍሳቸውን ይማረውና - የእናቷ ነበር፡፡ እናቷ ከከፈላቸው  ሁሉ ይተኙበት የነበረው አልጋ አሁንም አለ፡፡ አሁንም የመክፈል አቅም ካላቸው ጋር ልጅቱ ትተኛበታለች፡፡ ልጅቱ በተረገዘችበት የሽቦ አልጋ ላይ ነው እንጀራዋን እየጋገረች ያለችው፡፡
ከመወለዷ አስቀድሞ በተገዛ መስታወት ዐይኖቿን ፈለገቻቸው፡፡ ዐይኖቿ ትናንሽ ስለሆኑ አጨንቁራ የምታይ ያስመስላታል፡፡ መልኳን ትክ ብላ እያየች፣ እናቷ በሕይወት ብትኖር ኖሮ ምን ልትመስል ትችል እንደነበር ማሰላሰል ያዘች፡፡
እናቷን ማሰብ ስትጀምርና ሆድ በሚያስብሱ ነገሮች ስትከበብ፤ መስታወት ፊት ትቆምና መልኳ ላይ አፍጥጣ ስትነጫነጭ ታመሻለች፡፡