2013 ሴፕቴምበር 20, ዓርብ

እጃችሁ በደም ተነክሩዋል….



እጃችሁ በደም ተነክሯል….
…ወደ ኦሪታውያኑ ዘመን ልመልሳችሁ፤ ከዚያ ዘመን ውስጥ ፈርኦንን፣ ሙሴንና ኢያሱን እናንሣ፤ እነዚህን ሰዎች ደግሞ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ እንፈልጋቸው፤ የእነዚህ ቢጤዎች ናቸውና ዛሬ እንደጨቋኝ ገዢ ተቆጥረው የወቀሳ ናዳ የሚዘንብባቸው፤ የእነዚህ ቢጤዎች ናቸውና ዛሬ ከጭቆና ነፃ እንዳወጡን ተነግሮ የሰማዕት ሀውልት እንዲቆምላቸው የሚደረገው፤ የእነዚህ ቢጤዎች ናቸውና ዛሬ በህይወት ኖረው÷ ከወንድሞቻቸው የተቀበሉትን የትግል ዓርማ ከፍ አድርገው የተስፋይቱን ምድር እንዲጐበኙ የፍትህ አምላክ ስለ ፈቀደላቸው ደስ የምንሰኝባቸው!
…‹ያ› የምንለው ትውልድ ተገልጦና ተነብቦ የማያልቅ መጽሐፍ እየሆነ ነው፤ ውለን ባደርን ቁጥር ተድበስብሰው የታለፉና ተቆፍረው የተቀበሩ ጉዶችና ገድሎችን እያደመጥን ነው፤ ያንን ትውልድ የሚያጀግኑ መዝሙሮች መስማት ብቻ ሳይሆን፤ የትውልዱን አካሄድ የሚነቅፉ ብዕረኞችም በየህትመት ሚዲያው ብቅ ብቅ እያሉ ነው፤ እነዚህ ብዕረኞች ትውልዱን ጀብደኛ ነበረ ነው የሚሉት፤ ከውጭ ሀገር የተኮረጀ ርዕዮት ይዞ ስለተነሣ ነው ተሰናክሎ የወደቀው ነው የሚሉት፤ ሕዝቡ የኔ ነው ብሎ የሚያምንበትን አምላኩን ከልቡ ለማስወጣት ይታገል ነበር ነው የሚሉት፤ ብዙ የሚሉት ነገር አላቸው፤ እንዲህ በማለታቸው አንዳንድ የያ ትውልድ አባላት ተቺዎቻቸውን ተቆጥተዋል፤ ሣታውቁን ነው የምትዘባርቁት ብለዋል፡፡
          ጉዳዩ አጨቃጫቂ ነው፤ ክርክርና ንትርኩም የሚቀጥል! ያ ትውልድ ሜዳው ሰፊ ነው፤ በዚህ ሰፊ ሜዳ ላይ በ1960ዎቹና 70ዎቹ መጀመሪያ የነበሩ ወጣቶች ተጋጥመውበታል፤ ተጋጣሚዎቹ የማይከሰስና የማይወቀስ የሆነውን ንጉሳዊ አገዛዝን ገርስሰው ጥለዋል፤ የማይነካውን ከደፈሩ በኋላ ግን እርስ በርስ ተበላሉ፤ እርስ በርስ ተዋዋጡ፤ አብዮቱ ‹አፋጀሽኝ›ን ሆነ፤ መቧደናቸው ቀጠለ፤ ሞት፣ ስደት እና እስር የሁሉንም ቤት ለመጐብኘት ትጥቁን አጠበቀ፤ ደርግም፣ ኢሕአፓም፣ ሕወሓትም፣ መኢሶንም… ወዘተርፈው በሙሉ ልቡን ወያኔ አደረገ፤ ሸፈተ፤ ከተማውም ገጠሩም ዱሩም ገደሉም የእዚህ ትውልድ መሸሸጊያ ሆነ…

…አምናለሁ፤ እያንዳንዱ ዘመን የራሱ የሆነ ፈርኦን አለው፤ የራሱ የሆነ ሙሴ አለው፤ የራሱ የሆነ ኢያሱ አለው፤ በየትም ቦታ፤ በየትም አገር፤ በየትም ቤት፡፡
ኢትዮጵያ በጭቆና ስር ነበረች፤ እንደግብፃዊው ፈርኦን በፍርሃት እያራደ ጉልበት የሚበዘብዝ፤ ለሰራተኛ ደመወዙን ለመክፈል የሚያመነታ፤ የጭንቅ ጅራፍን እያስጮኸ በነዋሪው ላይ ድንጋጤን የሚዘራ መንግስት ነበራት፤ ደርግ የተባለ፡፡ ይህ ፈርኦናዊ መሪ የተረገጠ፣ የተናቀ፣ ራሱን ለለውጥ ያነሣሣ ቢሆንም በአጋጣሚ ለሀላፊነት የበቃ ነው፤ ጨቋኙን ጥሎታል፤ ቢጥለውም ግን የትውልድ አባሎቹ ለሚያነሱት ጥያቄ መልስ የመስጠት አቅም አልነበረውም፡፡
ስለዚህ እምቢ ባዮች ቀበቶአቸውን ማጥበቅ ነበረባቸው፤ ከፈርኦናዊው ደርግ ጋር ትንቅንቅ መግጠም ነበረባቸው፤ ራሳቸውን ለአንድ ለታላቅ ዓላማ ማጨት ነበረባቸው፤ የመረጡት ዋጋ ህይወት የሚያስከፍል መሆን ነበረነት፤ ልክ እንደ ሙሴ፡፡
በ‹ያ ትውልድ› ዘመን የነበሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሙሉ፤ ልክ እንደ ሙሴ፤  ባርነት የተጫነውን፣ ነፃነት የተራቆተውን፣ እንዳይናገር እንዳይፅፍ የተከለከለውን ሕዝብ መምራት ይጠበቅባቸው ነበር፤ በዚህ የትግል ወቅት መጠፋፋት፣ መገፈታተር እና በአካሄድ ከመንጋው የተለየ የሆነውን ማስወገድ የሚጠበቅ ነው፤ ለራስ ወገን፣ ለራስ ስልጣን፣ ለራስ ፓርቲ አድልቶ የሌሎችን ህይወት ማጨለም የያ ትውልድ አንዱ መለያ ባህርይ ነው፤ ይህንን ያደርጉ የነበሩት ደግሞ የየፓርቲው ሙሴዎች ናቸው ብለው የሚወነጅሏቸውም አሉ፡፡
ሙሴዎቹ ዘመን ካለፈ በኋላ፤ እናንተ የጫራችሁት እሣት ነው፤ ደርግን ለብልቦት፤ በወረወራችሁት ነበልባል መልሶ የፈጃችሁ ቢባልም አይቀበሉትም፤ ጥፋተኝነትና ፀፀት ከልባቸው ደጅ አያልፍም፤ የደም መፋሰሱ ሁሉ ምክንያት ‹ፈርኦን ነው› ይሏችኋል፤ መንግስቱ ኃይለማርያምና መሰሎቹ ናቸው ይሏችኋል፤ ክፍሉ ታደሰ እንኳን በአንድ ወቅት ምንድን ነበር ያለው?...
‹….እኛኮ የጦርነት አዋጁን አላወጣንም፤ በኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ላይ ጦርነት አላወጀንም፤ ጦርነቱ እንዳይታወጅና ሰላማዊ ትግሉ እንዲቀጥል ጥረት አድርገናል፡፡ ፈርተን ግን ትግሉን አላቆምንም፡፡ መታገል ደግሞ ወንጀል አይመስለኝም ተቻኩለን […] ቃታ አልሳብንም፡፡ እስኪሳብብን ጠብቀናል፡፡› (ጦቢያ መጽሔት ቅጽ 5 ቁጥር 4)
ይሄ አንዱ ስለአንዱ የሚናገረው ነው፤ ከሳሹም ተከሳሹም ምላሻቸው ተመሳሳይ ነው፤ ሁሉም የያ ትውልድ አባላት ራሳቸውን ሙሴ አድርገው ነው የቆጠሩት- የሀገሪቱ የቁርጥ ቀን ልጅ፤ ተራማጅ፤ ሀገር ወዳድ፡፡
የሞተውም የተገደለውም፤ የተሰደደ አሳዳጁም፤ የታሰረ አሳሪውም… አብዛኛው ለማለት በሚያስችል መልኩ ለሀገር ነው የኖረው፤ ለሀገር ነው የሞተው፤ የሚቆምለትና ህይወቱን አሣልፎ እንዲሰጥ የምታደርግ ባንዲራ በልቡ ውስጥ ትውለበለብ ነበር፤ በፈርኦን አገዛዝ ስር ለነበሩ፤ በእግሮቹ ለሚረገጡ ንፁሃን ዜጐች ጊዜያቸውን ሰውተዋል፤ ህዝቡ ወደ ዴሞክራሲና ፍትህ ሀገር ይሄድ ዘንድ የተስፋይቱን ምድር ተሳልሞ ነፍሱን በሃሴት ይሞላ ዘንድ ብዙ ወንዞችን ተሻግረዋል፤ በዚህ ውሃን ከአለት ለማፍለቅ በሚያስመኝበት የበረሃ ጉዞ ውስጥ፤ የህዝቡ ጥያቄ ቅጥ ከማጣቱ የተነሣ-የየፓርቲ መሪዎቹ ብዙ ተጐሣቁለዋል፤ ተፈትነዋል- ልክ ሙሴ እንደሆነው! አምላኩን አምርሮ እንደጠየቀው፡፡
‹…የዚህን ህዝብ ሁሉ ሸክም የጫንህብኝ ምን አስቀይሜህ ነው? ይህን ሁሉ ህዝብ የፀነስሁት እኔ ነኝን? እኔስ ወለድሁትን? ታዲያ ሞግዚት ሕፃን እንደምትታቀፍ በክንዴ ታቅፌ ለቀድሞ አባቶቻቸው ትሰጣቸው ዘንድ በመሓላ ቃል ወደ ገባህላቸው ምድር እንዳስገባቸው የምትነግረኝ ለምንድነው? …እጅግ ከብዶኛልና ይህን ሁሉ ህዝብ ብቻዬን ልሸከም አልችም…› (ዘኁልቁ 11÷10)
ለኦሪታዊው ሙሴ የተስፋይቱ ምድር ወይም ለአባቶቹ በመሓላ ቃል የተገባላቸው ምድር ‹ከነዓን› ናት፡፡ ለኛዎቹ ለያ ትውልድ አባላት፤ የሚመኟት አገር፤ ሊሰሩዋት የሚፈልጓት አገር፤ በብሄር ብሄረሰቦች እኩልነት የምታምን ናት፤ የዴሞክራሲን ትርጉም በህይወቷና በኑሮዋ የምትተገብር ናት፤ ህዝብ የመረጠው መሪ ስልጣን ላይ እንዲወጣ የምታበረታታ ናት፡፡ እናም እነዚህንና እነዚህን የመሳሰሉ መብቶችን ስለምታስጠብቅ ሊኖሩባት በብዙ ደክመዋል-
ግና እነዚህ ሙሴዎች የተመኟትን አገር አላገኟትም፤ የተስፋይቱን ምድር አልጐበኟትም፤ ለምን ቢባል- የፍትህ አምላክ- የዴሞክራሲ ጌታ- እጃቸው በደም መነከሩን ልብ ብሎ አይቷልና! ኦሪታዊው ሙሴ-ዕብራዊ ወንድሙ በአንድ ግብፃዊ ሲደበደብ አይቶ፤ ደሙ በቁጣ ፈልቶ፤ አካባቢውን ቃኝቶ ማንም አለመኖሩን አረጋግጦ ግብፃዊውን ገድሎ አሸዋ ውስጥ በመቅበሩ ምክንያት እጁን በደም አቆሽሿል፤ በዚህም የተነሣ የጓጓለትን ምድር አልረገጠም፡፡ የያ ትውልድ አብዛኛው አባላትም- በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ- እጃቸው ላይ ደም አለ፤ አውቀውም ይሁን ሳያውቁ፤ ለሥልጣን ጥማትም ይሁን ለፓርቲያቸው ሕልውና ሲሉ ከዓይን ተሰውረው ‹ወንድሞቻቸውን› ገድለው ቀብረዋል፤እናም እንዲህ እላለሁ…… የተስፋይቱን ምድር ይመኟታል እንጂ አያገኟትም!
የሙሴ ዘመን እያለፈ ነው፤ የኢያሡ ዘመን ደግሞ እየመጣ…
ኢያሡ የሙሴን መንገድ የጨረሰ ነው፤ የያ ትውልድ አባላት በብዙ ነገር መምህራን ሊሆኑን ይገባል፤ የዘሩት ሁሉ ሲበቅል የጣዱት ሁሉ ሲበስል የማየት እድል ባይገጥመንም፤ ለዓላማ መቆም ምን ማለት እንደሆነ አሳይተውናል፤ ጊዜን፣ ጉልበትን፣ ገንዘብንና ዕውቀትን ሳይሰስቱ ሀገርን ማገልገል ምን ማለት እንደሆነ÷ ከየ ፓርቲዎቹ ሙሴዎች ተምረናል፡፡
የአብዛኞቹን ሙሴዎች መውደቂያ ቦታ ሳናውቅ፤ መሞት መኖራቸውን ሳንለይ፤ እምን ጥሻ ስር አስከሬናቸው እንደተወዘፈ ሳይነገረን አመታትን አስቆጥረናል- እርግጥ ነው እነዚያ ሰዎች ለመመለክ በሚያበቃ መልኩ ስሞቻቸውን በተከታዮቻቸው ልቦና ውስጥ አስርገው አስገብተዋል… አሁን ሀገሪቷ የሚያስፈልጋት እጁን በደም ያልነከረ ትውልድ ነው፤ የያ ትውልድ አባላት እጆቻቸውን አንስተው ጭንቅላታችን ላይ ጭነው እንዲባርኩንና በጥበብ መንፈስ እንዲሞሉን እንጂ በድሮ በሬ አጥምደው እንዲያርሱን መፍቀድ የለብንም፤ በአንዳንዶቹ ልቦና ላይ የቆየ -ከ35 ዓመት በላይ ያስቆጠረ የቂም ሂሳብ የማወራረድ ነገር ይታያልና!

2 አስተያየቶች:

  1. "አሁን ሀገሪቷ የሚያስፈልጋት እጁን በደም ያልነከረ ትውልድ ነው" exactly

    ምላሽ ይስጡሰርዝ
  2. ohh this thanks Endale .I was confused about this generation but the solution is easy if they think like this because History is like school if think solve the today problem!!

    ምላሽ ይስጡሰርዝ