2013 ኦገስት 16, ዓርብ

ምጣዱ



ከርቀት  
አንድ ሰባኪ ድምጹን አስጩሆ የመዝጊያ ጸሎት ሲያካሂድ ይሰማታል፡፡
“የዕለት እንጀራችንን ስጠን ዛሬ . . .”
“አሜን” አለች - ፈገግ ብላ፡፡ አልጋዋን ዐየችው - የዕለት እንጀራዋን የምትጋግርበት ምጣዷን፡፡
አሁን የምትኖርበት ክፍል - ነፍሳቸውን ይማረውና - የእናቷ ነበር፡፡ እናቷ ከከፈላቸው  ሁሉ ይተኙበት የነበረው አልጋ አሁንም አለ፡፡ አሁንም የመክፈል አቅም ካላቸው ጋር ልጅቱ ትተኛበታለች፡፡ ልጅቱ በተረገዘችበት የሽቦ አልጋ ላይ ነው እንጀራዋን እየጋገረች ያለችው፡፡
ከመወለዷ አስቀድሞ በተገዛ መስታወት ዐይኖቿን ፈለገቻቸው፡፡ ዐይኖቿ ትናንሽ ስለሆኑ አጨንቁራ የምታይ ያስመስላታል፡፡ መልኳን ትክ ብላ እያየች፣ እናቷ በሕይወት ብትኖር ኖሮ ምን ልትመስል ትችል እንደነበር ማሰላሰል ያዘች፡፡
እናቷን ማሰብ ስትጀምርና ሆድ በሚያስብሱ ነገሮች ስትከበብ፤ መስታወት ፊት ትቆምና መልኳ ላይ አፍጥጣ ስትነጫነጭ ታመሻለች፡፡
“ሁለ ነገርሽ የናትሽን ይመስላል” ይሏታል ጎረቤቶቿ፡፡ ጠየም ትላለች፡፡ የተስፋ መቁረጥ አመድ የተነሰነሰበት ትንሽዬ ፊት አላት፡፡ አንድም ቀን፣ አንድመ ሰው ይሄ ነገርሽ ሲያምር ብሎ አሞካሽቷት አያውቅም፡፡
መስታወቱን ከግርግዳው ጋር አሳሳመችው፣ በቀድሞው ቦታው፡፡
ለባብሳለች፤ ተኳኩላለችም፡፡
እየጨለመ ነው፡፡ አልጋዋን ዓየችው፡፡ “ጾመኛዬ! አምላክ ካልጨከነብህ ዛሬ ትፈስክ ይሆናል” አለችው፡፡ አንሶላዋ የወንድ ጠረን ካሸተተ ሁለት ሦስት ቀን አልፎታል፡፡ አንዳንዴ እንዲህ ነው፡፡ የተጠቃሚው ቁጥር ከሚፈለገው በታች መሆኑ ቀርቶ የሌለ ያህል ይሆናል፡፡ ምንም!
አጉተመተመች፡፡
‘የዕለት እንጀራችንን ስጠን ዛሬ . . .’
ደጅዋ ላይ ቆመች፡፡
ከሷ ቤት ትይዩ ‘ስልክ እናስደውላለን’ የሚል ጽሑፍ መስኮቱ አንገት ላይ ያንጠለጠለ ትንሽ የሸቀጣሸቀጥ ሱቅ አለ፡፡ ቁጥሩን በአግባቡ የማታውቀው ስልክ አላቸው፡፡ ደውላበት አታውቅም፡፡ ተደውሎላትም አያውቅም ነበር፡፡
ነበር፡፡ በደጇ በተመላለሰ ቁጥር ሰላምታ ይሰጣት የነበረ አንድ መምህር ግን ደወለላት፡፡ የደወለላት ቀን እንዴት ነበር የደነገጠችው? ለመጀመሪያ ጊዜ በቀጭን ሽቦ ተሽሎክልኮ ወደ ጆሮ የሚገባ ድምጽ ስትሰማ . . . ለመጀመሪያ ጊዜ ድምጿን በስልክ ስታሰማ . . . ለመጀመሪያ ጊዜ የስልክ እጀታ ከንፈሯንና ጆሮዋ ሲደባብስ . . . እንደዚያ ቀን ተደስታ አታውቅም፡፡ ስትፍነከነክ አመሸች፡፡
እሷ እስከምታውቀው ድረስ - ነፍስ ካወቀችበት ጊዜ አንስቶ፣ በዙሪያዋ ካሉ ሴቶች እሷ ናት እንዲህ ያለ ዕድል ለመጀመሪያ ጊዜ የገጠማት፡፡
በስልክ የሰማቻቸው ቃላት እንደ ውብ ዝማሬ ከጆሮዋ አልጠፋ አሉ፡፡ “. . . ቅዳሜ ከሰዓት በኋላ እመጣለሁ፡፡ . . . እሺ? . . . ጫት አመጣና ስንቅም እናመሻለን”
“በሴተኛ አዳሪዎች ችግር ዙሪያ ፕሮጀክት እየቀረፅኩ ነው፡፡ ስፖንሰር ካገኘን የተሻለ ሕይወት መኖር የምትጀምሪበት ቀን እሩቅ አይሆንም፡፡ ራስሽን ጠብቂ፡፡ እሺ?!” ይላት ነበር . . .
ስለ እናቷ የምታብሰለስልባቸው ሰዓታት ብዙ ቢሆኑም መምህሩን ግን ሳታስበው የዋለችበት ቀን መኖሩ አይታወሳትም፡፡ በተለይ የስልክ ድምጽ በጮኸ ቁጥር  . . .
ዐይኗን ደጇ ላይ ወደሚገኘው ሱቅ በወረወረች ቁጥር . . .
“ምስኪን . . . ” አለች፣ እያሰበች ያለችውን ነገር ለመርሳት እየሞከረች፡፡
አሁን የሥራ ሰዓት ነው፡፡
መሰሎቿን ዐየቻቸው፡፡ እነሱም እንደሷ ዝግጁ ናቸው፡፡ ከሬሳ ሣጥን የሚሰፋ በማይመስል ክፍሎቻቸው ደጅ ላይ አቋቋማቸውን አሳምረው ቆመዋል፡፡ ቀያይ ብርሃናት በየበሩ ውጭ ምን እየተደረገ እንደሆነ ይታዘባሉ፡፡
ሙዚቃው ይጮሃል - ዕጣኑ ይጨሳል - ሣቁ ደርቷል - ወሲቡም ይወሳባል፡፡
ከስንትና ስንት ጥበቃ በኋላ አንድ ወንድ መጣ፡፡
ፊቷን አበራችው፡፡
ዐየችው! ደረቷን፣ ግማሽ ጡቷን፣ እምብርቷን የሚያሳይ ልብስ ከወገብዋ በላይ ውሏል፡፡ ከታች አጭር ቀሚስ . . .
እያያት ነበር፡፡ ጨለማው ሰውነቱን ደብቆለታል፡፡ እሷም ምን እንደምትመስል አታስታውቅም፡፡ ጭኗ ብቻ ነው ደምቆ የሚታይ፡፡ እንቁልልጬ ብሎ የሚያስጎመጅ. . .
ወጣቱ የሴት አምሮት እረፍት ቢነሳው ነው፣ ይህን “ሥርዓተ . . . ” ያለማቋረጥ የማከናወንበትን ስፍራ ለመሳለም ልቡን ያነሳሳው፡፡
መለስ ቀለስ ብሎ አካባቢውን መቃኘት ያዘ፡፡
ገንዘባቸውን ለዝሙት የሚመነዝሩ አመንዝራዎች እየተጣደፉ የሚጎርፉበት ሰዓት ነው፡፡
ወደ ፊቷ እየመጣ ያለውን እግር ስታይ ገባች፡፡
ተከተላት፡፡
ለአዳር ነው የሚፈልጋት፡፡
ዋጋዋን ነገረችው፡፡
ውድ አልነበረም፡፡
አረቄ የያዘው ጠርሙስ - በመለኪያዎች ተከብቦ በትንሽዬ ጠረጴዛ ተጭኖ ጥጉን ይዟል፡፡ ረዘም ያለ ቡራቡሬ አንሶላ አልጋውን ጋርዶታል፡፡ ከጎን በኩልም ግርግዳ ላይ የተሰካው ምስማር የነከሰ ፎጣ ተንጠልጥሏል፡፡ የፎጣው ጫፍ ቆሽሿል፡፡ እጅ የሚበዛበት ስፍራ . . . እሷም እንደዚያ ናት፡፡
. . . አንዱ ጥግ በሸክላ የተሰራ ምድጃ ይታያል፡፡ ሆዱ ላይ የተበተነው ዕጣን ከፍሙ ጋር ተባብሮ ቤቱን አውዶታል፡፡ ሽታውን አልጠላውም፡፡ ግራሶ ግራሶ የሚል ጠረኑን አባርሮለታል፡፡
“ምንድነው? . . . ምን ተፈጥሯል?” አለ፣ ጆሮውን ወደ ውጭ እየተቀሰረ፡፡ እሱ ካለበት ክፍል ቀጥሎ ያለች አንዲት ሴት ጮክ ባለ ድምጽ ስትሳደብ ይሰማል፡፡
“. . . እኔ አንችን አይደለሁም፡፡ ምድረ ገንገበቱን የማስተናግድ! እሱም ቢሆን የለፋ ቆዳ የመሰለውን ጡቶችሽ ሳይዳብስ ነው እንትፍ ብሎብሽ የሚወጣ! . . . ስሚ! ደግሞ እግዜራችን ለእኔ ያለው እንጀራ ይሻግታል እንጂ ማንም አይቆርሰውም! ወስደሽብኝ ሞተሻል. . . ”
“ሁልጊዜ ነው እንዲህ የምትሳደበው?” አለ ጨዋታ ለመጀመር ያህል፡፡ “ጎረቤትሽ ተነጫነጭና ተናካሽ ከሆነሽ እንዴት ሆናችሁ ነው የምትኖሩት?”
“አላውቃትም፡፡ ጎረቤቴ አይደለችም” አለችው፣ በርዋን እየዘጋጋች፡፡
“ማለት . . .”
“አልጋውን ተከራይታ ነው፡፡ ነገ ደግሞ ሌላ ሴት መጥታ ትተኛበታለች ታስተኛበታለች”
“አከራይዋስ?! ማለቴ ለምን እሷ አትሰራበትም?”
“በእድሜ ገፋ ስላለችና ስለሚያምማት ገበያዋ ቀዝቅዟል፡፡ አንድ ወንድ ገብቶ በር ባዘጋ ቁጥር ግማሽ ሂሳብ የሷ ነው - የአከራይዋ፡፡ . . . የእናቴ ጓደኛ ነበረች”
“ያንችም አልጋ ተከራይቶ ያውቃል?” አላት ቂጡን አልጋው ላይ እያሳረፈና የጫማውን ክር እየፈታ፡፡
“አዎ”
“ለምን ያህል ጊዜ?. . . ”
“ከአስራ አምስት ዓመታት በላይ . . .”
“ዓመታት?!” ያልኩትን አልሰማችም ልበል? ብሎ ማለት የፈለገውን ለመጠየቅ ቀና ሲል ልብሶቿን ስልት ባለው ሁኔታ እያወላለቀች መሆኗን ዐየ፡፡
ገላዋን ሲያይ ቀበቶውን ፈታ፡፡
በጣም ርቦት ነበር . . . በጣም፡፡
አልጋ ላይ ወደቁ፡፡
ጎረሣት፡፡
ሆነም፡፡

“ፍቅር ይዞሽ ያውቃል?!. . . ” አላት ወሬ ለማውራት ያህል፡፡
“እ?”
“ፍቅር ይዞሽ አያውቅም?!
“መምህሩ ወንድሜ ነበር” አለችው - እሷ የምትለውን መመህር የሚያውቅ ይመስል፡፡ መምህሩ እንደ ወንድም ነበር የሚያያት፡፡ ያ ሁሉ ጊዜ አብሯት ሲውል - አልጋዋ ላይ እስኪመረቅኑ ድረስ ይቅሙበት ነበር እንጂ ተኝተውበት አያውቁም ነበር፡፡ የሥራ ሰዓት እስኪደርስ - አፉን ተጉሞጥሙጦ እስኪወጣ፡፡
“እኔና በዙሪያዬ ያሉ ሰዎች የተሻለ መኖር ስለምንችልበት ዘዴ ዕቅድ ሲነድፍ ነበር የሚያመሸው”
“ላልጠየቅኩሽ ጥያቄ ነው እንዴ መልስ የምትሰጪው?”
“ደግ ነበር፡፡ ምስኪን የደሃ ልጅ . . .”
“ማንንም አፍቅረሽ አታውቂም ነበር ማለት ነው?”
“ለማስተማር ገጠር ሲሄድ አውቆብስ ተራ መጥተሽ ሸኚኝ፣ ሲለኝ እምቢ ስላልኩት ሁልጊዜ ይከፋኛል፡፡ ግንኮ ሸኝቼዋለሁ፡፡ ስሸኘው ግን አላየኝም፡፡ እንዲያየኝም አልፈለኩም እንጂ መኪና ውስጥ ገብቶ አውቶብስ ተራን እስኪለቅ ድረስ እያየሁት ነበር”
በመጨረሻው ሰዓት እሱ ከእሷ ጋር በመታየቱ በወዳጆቹ ዐይን አንሶ የሚታይ ስለመሰላት ነው ያልሸኘችው፡፡
“ተፈቅረሽም አፍቅረሽም አታውቂም ማለት ነው?”
“ወንድሜ ነበር” እንደ ወንድም ሊታይ የሚችል ወንድም ማግኘት ለእሷ ከአምላክ ጋር የማውራትን ያህል ነው፡፡ የሚፈቀር ሞልቷል፡፡ የምትፈቀር ሴት ሆኖ መገኘትም አይከብድም፡፡ እንደ እሷ ላለ ብቸኛና ባይተዋር ግን መመህሩ ትልቅ ሰውና ታላቅ ወንድም ነበር፡፡
“የመስማት ችግር እንዳለበት ሰው ነው መልስ የምትሰጪው . . .”
እንደገና አንሶላውን ያለፉት ጀመር፡፡ “ለምን ቡና ቤት ተቀጥረሽ አትሰሪም?” አላት፡፡ ባመነጨው ሃሳብ ኩራት እንዳደረበት ግልፅ ሆኖላታል፡፡
“አልፈለግሁም”
“የተሻለ ይከፍሉሽና . . .”
“አልፈለግሁም”
“እዚሁ ያረጀ ቤት ውስጥ ከመኖር . . .”
ቁጣዋን ልትደብቀው ሞከረች፡፡
“ውድ ከሚያስከፍሉት በምንም አታንሺም”
ዝም፡፡
በልቧ ግን ‘ይህንን ቤት የምለቅቀው ይመስልሃል? አላደርገውም፡፡ የሚፈልገኝ ወደምገኝበት አስመጣዋለሁ እንጂ! . . . አውቃለሁ ቤቴ ጠባብ ናት - ሁለት አልጋ አታስዘረጋም፡፡ ቢሆንም ለኔ ትሰፋኛለች፡፡ እናቴ የወለደችኝ ዕለት የሞተችበት ክፍል እንደሆነ ብነግርህስ ምን ይሰማህ ይሆን?’
“ምን ሆንሽ?” ከርደድ አጠር ያለ ፀጉርዋን እየደባበሰ፡፡
“ምነው?”
“ዐይንሽ እንባ አርግዟል፡፡ የሆንሽው ነገር አለ?”
በአሉታ አናቷን ነቀነቀች፡፡
“ደግሞ መማር ነው የሚያዋጣሽ፡፡ አንጎልሽ ለእውቀት ክፍት ይመስላል፡፡ ለምን አትማሪም?”
ከስምንተኛ ክፍል በላይ ትምህርቷን አልቀጠለችም፡፡ ‘ወላጅ አምጪ’ ትባል ነበር በየጊዜው፡፡ ከመምህሮቿ ጋር መግባባት አልቻለችበትም ነበር፡፡ የምትወስደው ወላጅ ስላላነበራት በየጊዜው ማልቀስ ነበር ሥራዋ፡፡ “ፊደል - ዳገቷ” ነበር ቅፅል ስሟ፡፡ ሚኒስትሪን ሦስት ጊዜ ከወሰደችው በኋላ ትምህርት ቤት የመመላለሱን ነገር እርግፍ አድርጋ ተወችው፡፡
ብድግ አለችና የአረቄው ጠርሙስ ጨበጠችው፡፡ በአንዱ መለኪያ ቀዳችበት፡፡ ሙሉ ነበር፣ አጋመሱት፡፡
ጭ-ር-ር-ር-ር- የሚል የስልክ ድምጽ ሰፈሩን ሲረብሸው - ድንግጥ ብላ - ሲሰርቅ እንደተደረሰበት ህፃን ተረብሻ - ነቃ ስትል ዐያት፡፡
“ምነው?” አላት፡፡
“ስልኩ!
“እ? . . .” አለ ምን ማለት እንደፈለገች ግራ ገብቶት፡፡
“ተደወለ”
“ላንቺ ነው?” አላት፡፡ ‘እየመጣሁ ነው’ ብሎ፤ እየመጣ መሆኑን ቀደም ብሎ ደውሎ የሚያሳውቅ ደንበኛ ይኖራት ይሆን? ብሎ እያሰበ፡፡
“መምህሩ ብቻ ነው ደውሎልኝ የሚያውቀው” አለች ሆድ በሚያባባ ድምጽ፡፡
“እና . . . እሱ ነው ማለት ነው?!
“በመምህራን ማሰልጠኛ ተቋም ተመርቆ ገጠር ሊያስተምር ከተላከ ዓመት አልፎታል፡፡ ከሄደ ድምጹን ሰምቼ አላውቅም”
“ታዲያ ምን አስደነገጠሽ?”
“እኔንጃ! ሁልጊዜ የስልክ ድምጽ ስሰማ ሁል ጊዜ እንዲህ ያደርገኛል፡፡”
ፀጥታ ሆኗል - ፀጥ፡፡
“አውሪኝ!
“ስለምን?”
“በቃኣ! አለ አይደል . . . ስለሆነ ነገር ዝም ላለማለት ያህል . . .” አላት አረቄውን ወደ አፉ እያስጠጋ፡፡
“ቀዝቃዛ ነሽ ወይስ ስሜት አልሰጠሁሽም? ወይስ ለሁሉም ወንድ እንዲህ ነሽ? . . . ስለምን እንደሆነ አላውቅም እንጂ በጥልቀት እያሰብሽ ነው”
ከወንድ ጋር ስትተኛ እንደዚሁ ናት፡፡ ወላጆቿን ስለማታውቃቸው በአሁኑ ሰዓት ጭኗ ላይ ያስጋለበችው ጉብል የእናቷን ማኀፀን የተጋራ ይሁን አይሁን ምንድነው ያላት መረጃ? ወይም ከአንድ አባት ዘር የተከፈሉ መሆናቸውን ሳያውቁ እግራቸው ተቆላልፎ እንደሆነስ? . . . ይቀፍፋታል፡፡
ሞቅ ሲላት አንደበትዋ እየተኮላተፈም ቢሆን ሕይወቷን ተረከችለት፡፡
ሃያ አንድ ዓመት ከሞላት መንፈቅ አላለፈም፡፡ ግና ነፍስ ካለቀችበት ጊዜ ጀምሮ ዘመዷ ነኝ የሚል አልመጣም፡፡ አለሌ ከነበረው ከታላቅ እህቷ ባል ጋር አልጋ ላይ ስለተደረሰባት ነው፣ እናቷ ከዘመድ ወዳጅ የተቆራረጠችው፡፡
አልጋዋንና ቤቷን ለአስራ አምስት ዓመታት ያህል በሣምንት ለሁለት ሦስት ቀናት አራይተው - በተከራየበት ገንዘብ ደግሞ የዓመት ልብሷን የዕለት ጉርሷን የሚሸፍኑላት የእናቷ ጓደኛ የሆኑት ጎረቤቷ ነበሩ፡፡
አንድ ቀን፣ ‘እትዬ፣ እናቴ ዘመድ አልነበራትም?’ ብላ ስትጠይቃቸው ‘ሃገሩ የት እንደሆነ ጠፍቶኛል እንጂ፣ ወዳዲሳባ ጉዳይ ገጥሞት ሲመላለስ የሚጠይቃት ሰው እንደነበረ አስታውሳለሁ’ አሉዋት
‘ወንድሟ ይሆን ይሆናል ወይም አጎቷ!
‘የከንፈር ወዳጄ ነበር ብላ አስተዋውቃኛለች፡፡ ካገር ቤት ወዳጆቿ ሁሉ ፊቱን ያልመለሰባትና፣ አንገቱን ያልቀለሰባት እሱ ብቻ ነበር’
“ታዲያ የት ጠፋ? ከተወለድኩ በኋላ ብቅ ያላለው ሞቶ ይሆን?”
“ማን አውቆ ልጄ?! የቀብር ቀኗ ካለፈ በኋላ ዐይኑን ዐይቸውም አላውቅ!
እናቷን ዐይታት አታውቅም፡፡ ፎቶግራፏም እቤት ውስጥ የለም፡፡ የተወለደች ዕለት አይደል እናቷ ያረፈችው? “ከኔ አብራክ ነው የከፈልሽው” የሚል አባትም አልመጣም፡፡ የእናቷ ጓደኞች እየተቀባበሉ አሳደጓት፡፡ ለአቅመ - ወሲብ ስትደርስ የእናቷን ሙያ መተዳደሪያዋ ሆነ፡፡ የእናቷ ምጣድ ረሃቧን የምታስደነግጥበት ፈጥኖ ደራሽ ሆነ፡፡ ሰልችተዋት ስለበር የተቃወማት አልነበርም፡፡
ሆድ ይብሳታል፡፡ ባህር ላይ የምትንሳፈፍ ቅጠል የሆነች ይመስላታል፣ ከየትኛው ዛፍ ላይ እንደወደቀች ሳታውቅ ማዕበል የሚያንገላታት፡፡
“አላምንሽም!” አላት ታሪኳን ሰምቶ ሲያበቃ፡፡
“እንድታምነኝ አይደለም የነገርኩህ፣ የሆንኩትን የኋላ ታሪኬን እንድተርክልህ ውስጤ ስለገፋፋኝ እንጂ” አለችው፡፡
“በጭራሽ አላምንሽም!!” ሞቅታው ስለመጣ በጮክታ ነው የሚሟገታት፡፡ “ለመሆኑ እዚህ አንቺ ጋ፣ ዲሲ ለምን እንደመጣሁ አውቀሻል?”
“ምክንያትህ ምን ይረባኛል? ገንዘብ አልጣ እንጂ” በሚል ስሜት ትከሻዋን ሰበቀችው፡፡
“ባለቤቴን ካቀፍኳት ሦስት ወር ሞላኝ፡፡ አንድ ቤት እያደርን - እሷን የመቀምጨል ሕጋዊ መብቴን እናቷ ያለ አግባብ እየተጫኑኝ ነው፡፡ እናቷ ታመው ከገጠር ከመጡ ጊዜ ጀምሮ ከእሳቸው ጋር ነው ውላ እያመሸች፣ አምሽታም የምታነጋው፡፡ ታዲያ እኔ መፈንዳት አለብኝ? እ? ንገሪኝ እስኪ . . . ” አረቄውን አነሳ፡፡ ተጎነጨው፡፡
ባደረገው ነገር እንዳልተደሰተ፣ ህሊናው እንደናቀውና የገዛ ገላውንም እንደተፀየፈ ገባት፡፡
“እናታቸው አፈር ትብላ! . . . እኚህ የባለቤቴን እናት ሰበብ ፈልጌ ከቤቴ የማባርርበት መላ ልጣ? የማንም . . . ሞት የረሳት አሮጊት መፈንጫ ሆኜ የተከበረች ሚስቴን የመሳሚያ ጊዜና ቦታ ልጣ? በነገራችን ላይ ከማውቃቸው ሽርሙጦች ሁሉ ያንቺን ያህል በውሸት ራሷን ያሰለጠነች ሴት አጋጥማኝ አታውቅም፡፡ የተሻለ ዋጋ እንዲከፈልሽ ብለሽ የፈጠርሽው አንጀት የሚያባባ ልብ ወለድ ታሪክ እንጂ፣ የትኛውም ሴት አንቺ ኖርኩት የምትይውን ዓይነት ሕይወት ልትኖር አትችልም”
“እውነትህን ነው . . . ” አለችው፣ የጣቷን ጥፍር በጥርሷ እየቀነጣጠበች፡፡ “አንዳንድ ሰው ተረት የሚመስል ታሪክ ይኖረዋል”
ጥዋት ቀበቶውን ስያስር “ኧይ የእንጀራ ነገር! ደግሞ እንዲህም ተጀመረ?” ሲላት እሷም በልቧ እንዲህ አለችው፡፡
“አቤት! ይህ ምጣድ ስንቱን አስተናግዷል? የስንቱን ጠረን ታጥኗል? ነገ ደግሞ እንዴት ያለ ገላ ምን አይነት አመል ይዞ ይመጣ ይሆን?!

“ምንድን ነው ይሄ?” ትላንት ጎረቤት ከሆነ ሱቅ በዱቤ ኮንዶም ስትገዛ፣ ኮንዶም የተጠቀለለበት ወረቀት ከመሬት አንስቶ መያዙን አየች፡፡
ከሆነ መጽሐፍ የተገነጠለ ገፅ ነው፡፡ “ሆነ ተብሎ እንጂ በአጋጣሚ አይመስለኝም” አላት፡፡
“ምን?”
“ይህ ወረቀት በእጅሽ እንዲገባ የተደረገው . . . ላንቺና ለመሰሎችሽ የተፃፈ ደብዳቤ ይመስላል”
አቀበላት፡፡
አነበበችው፡፡
“ስትሞቺ የማያውቅሽ ባይተዋር ነው ጫር ጫር አድርጎ የሚቀብርሽ፡፡ የወዳጅ ዘመድ እጅ ሳይነካሽ፡፡ አንድ እንኳ ሰው አዝኖ ሳያለቅስልሽ፡፡ ያኔ ሁሉም የሚያስቡት እንዴት አድርገው ሬሳሽን በፍጥነት ወዲያ ብለው እንደሚገላገሉ ነው፡፡ በዚህ ሰፊ ዓለም ከሚርመሰመሰው ሕዝብ አንድ እንኳ የሰው ፍጡር ሊያስታውስሽ ከመቃብርሽ የሚሄድ የለም፡፡ እንዳልተወለድሽ እንዳልኖርሽ ስምሽ አብሮሽ ይቀበራል”
ሽርክትክት አድርጋ ቀዳደደችው . . .
ከእናንተ መካከል ኃጢያት የሌለበት የመጀመሪያውን ድንጋይ አንስቶ /ዘማዊቷን/ ይውገራት፣ ያለው ክርስቶስ መምህር ነበር አይደል? . . .
አንቺ ሴት ከሳሾችሽ ወዴት አሉ?
መምህራን ደስ ይሏታል፡፡ “ትለወጫለሽ አዲስ ታሪክ ይኖርሻል!!!” ይል የነበረው መምህር የሆነው ወዳጇ፣ “በቅርብ ቀን እመጣለሁ!” ካለ ምን ያህል ጊዜ ሆነው?!

3 አስተያየቶች: