2013 ሴፕቴምበር 19, ሐሙስ

ያልተቀበልናቸው (2)



ይኼ የ ‹ያ ትውልድ› ውጤት ነው፤ ከ1950ዎቹ ወዲህ (ከታህሳስ ግርግር በኋላ) በተፈጠረው የፖለቲካ ትኩሳት ሰበብ፤ እነ ጥላሁን ገሠሠ (ድምፃዊ) ለመጀመሪያ ጊዜ ከአማርኛ ቋንቋ ውጪ አይደፈር የነበረውን በኦሮምኛ ቋንቋ ዘፍነው በሸክላ አስቀረፁ፤ እነ መኃሙድ አህመድ (ድምፃዊ) የጉራጊኛ ዘፈን አስደመጡ፤ ቀስ በቀስ ሌሎች ተከተሉ፤ አፍ መፍቻ ቋንቋቸው አማርኛ ያልሆነ ደራሲዎች መነበብ ጀመሩ - ጸጋዬ ገ/መድህን ከአምቦ÷ ስብሃት ገ/እግዚአብሔር ከአድዋ÷ ሰሎሞን ደሬሣ ከወለጋ÷ ሳህለሥላሴ ብርሃነማርያም ከእምድበር÷ አማረ ማሞ ከሲዳሞ… በኢህአዴግ ዘመን ደግሞ አንዱን ብሄር መርጦ፣ አንዱን ማኅበረሰብ ለይቶ ራሱንም የተዘፈነለትን አካባቢም የሚያስተዋውቅ ድምጻዊ በዛ፤ ዘፈኖቹ በአብዛኛው ተመሳሳይና ተደጋጋሚ ይዘት ያላቸው (የሆነ ሰው፣ የሆነ ቦታ ሄዶ፣ የሆነች ሴት ዓይቶ፣ በፍቅሯ ተማርኮ ‹አንቺን ካገኘሁ አዲስ አበባ ለምኔ› የሚሉ፤ ከግጥሙ ይዘት ይልቅ ለአጨፋፈር ስልታቸው ቅድሚያ የሚሰጡ) ቢሆኑም፤ የተጫወቱት ሚና እና ሚዲያው የሚሰጣቸው ሽፋን ቀላል አይደለም፡፡ የኦሮሞዎች ‹እሬቻ›ን፣ የሲዳማዎች ‹ጨምበላላ›ን፣ የትግራይ ክልል አካባቢ ነዋሪዎችን ‹ሻደይ›ን ማክበራቸውም ጥሩ ነው -
 እዚህ ደረጃ ለመድረስ ጥርጥር የለውም ብዙ ዋጋ ተከፍሏል፤ ሆኖም ግን ነጠላ ዜማ ስለተለቀቀለትና አንድ ትውፊታዊ በዐሉ ስለተከበረለት አንድ ብሄር ማንነቱ ታወቀለት ማለት አይደለም፤ ይሄ ብቻ በቂ አይደለም፤ ማንነት በዳንስ ብቻ አይለካም፤ በብሄር-ብሄረሰቦች ቀን እንዲታደሙ ስለተጋበዙ ብቻ ሙሉ ማንነታቸው ታውቆላቸዋል ማለት ስህተት ነው፤ ማንነት በጥልቀት የሚታይ መሆን አለበት እንጂ፤ እንደ ብሄራዊ ቴአትር ባለ አገር ፍቅር መድረክ አኗኗራቸው በጨረፍታም ቢሆን የሚታይ መሆን አለበት እንጂ፤ እንዲሁ ስለተዘፈነላቸውና ዳንስ ማሳያ መድረክ ስለተዘረጋላቸው የችግሮቻቸው ቀዳዳ ተደፈነ ማለት አይደለም፡፡

  በብሄር ብሄረሰቦች ቀን ‹ጥሩዋቸው እስኪ እነዚያን ጥቁሮች! ሞቅ ሞቅ ያድርጉት በዐሉን› ተብለው የቀረቡ ነው የሚመስሉት፡፡ ይሄ አይደንቅም ወይም አይደንቀኝም፤ በበዓል ቀን የቅርብ ብቻ ሳይሆን የሩቅ ሰውም ይጋበዛል፤ ወዳጅ ዘመድ ይታደማል፤ ፊታውራሪውም፣ በረንዳ አዳሪውም ይጠራል፤ የነዚህ የተናቁ፣ የተረሱ፣ የማናውቃቸውና እንደ መጤ የምንቆጥራቸው ኢትዮጵያውያን በዓመት አንድ ቀን ‹በየማጌጫችሁ ተሽሞንሙናችሁ ቅረቡ› ብሎ መጋበዝ ‹የእኩልነት መብታቸው መረጋገጡን› አያሳይም፤ የሚያስፈልገው እነሱን ለአደባባይ ማብቃት ነው፤ የተዘጋባቸው የዕውቀት፣ የስልጣንና የስልጣኔ ብቻ ሳይሆን የሰብዓዊ መብቶች በር እንዲከፈትላቸው ማድረግ ነው፡፡
አዲሳባ ፒያሳ እምብርት ላይ አንድ ማስታወቂያ አይቼ ነበር ‹ስክሪን› ላይ የሚተላለፍ፡፡ ስክሪኑ ላይ የአማራ አለባበስ የለበሰች አንዲት ሴት ታልፋለች - ‹አማራ ነኝ፤ በአማራነቴ እኮራለሁ› ትላለች፤ ትግሬዋም፣ ኦሮሞዋም፣ ሶማሌዋም፣ ሀደሬዋም… ሁሉም እየመጡ ይሄዳሉ፤ የብሄራቸውን ስም ጠቅሰው ‹እኮራለሁ!› የሚል መልእክት አስከትለው፡፡ ከዚያም አንዲት ሴት ትመጣለች (?)፤ ‹ደቡብ ነኝ፤ በደቡብነቴ እኮራለሁ› የምትል፡፡ ያነበብኩት ቀን በጣም ነው በፌዴሬሽን ምክር ቤቱ ያፈርኩት - ደቡብ የብሄር ስም ነው እንዴ? ወይስ ማን የሁሉንም ስም ሲዘረዝር ይውላል ለማለት ነው?... ደቡብ የአቅጣጫ ስም ነው፤ በደቡብነቴ እኮራለሁ ማለት ምንድነው? አንዲት ሴት እንዴት ከ45 ያላነሱ ብሄሮችን ወክላ ትቀርባለች? ይኼ የተወሰኑ ሰዎችን ስም ጠቅሶ የተቀሩትን ወዘተረፈ ብሎ ከማጠቃለል በምን ይተናነሳል?)
 …ኢትዮጵያ ውስጥ እጅጉን ከሚደንቁኝ ነገሮች መካከል፤ ከጋምቤላ አካባቢ የሚመጡ ሰዎችን የምናይበት ዓይን የተንሸዋረረ መሆኑ ነው…
አንድ ቀን÷ ከአንድ የቅርብ ወዳጄ ጋር አመሸሁ፤ ምሽቱ እየገፋ ሲሄድ፤ እኔ ደግሞ ሌላ የማውቀው ሰው ገጠመኝና የናፍቆት ሰላምታ ስለዋወጥ፤ ሰላምታው የረዘመበት ወዳጄ ‹መጣሁ› አለኝና ከወንበሩ ተነሣ፤ ከኛ ፈንጠር ብሎ ወደተቀመጠው ሰው በአገጩ አመላከተኝ፤ ሰውየው ጥቁር ነው፤ ብቻውን ቢራውን ይዞ እየተዝናና ነው፤ ዓይኑን በመደነስ ላይ በሚገኙ ወይዛዝርት ላይ አነጣጥሯል፤ ወዳጄ ‹መጣሁ እስኪ፤ ይህን ጥቁር አፍሪካዊ ላዋራው፤ አጋጣሚውን በመጠቀም የእንግሊዝኛ ቋንቋ ችሎታዬን ላሻሽል› አለና ሄደ፤ የሚነጋገሩት ይሰማኛል፤ ወዳጄ ጥቁሩን ሰው ለማጫወት በብርቱ እየተጋ ቢሆንም፣ ከየት እንደመጣ ቢጠይቀውም፣ ኢትዮጵያን እንዴት እንዳገኛት ቢያነጋግረውም፣ የወይዛዝርቱ ዳንስ የፈጠረበትን ስሜት እንዲያጫውተው ቢጐተጉተውም… ጥቁሩ ሰው ግን አልመለሰለትም፡፡ በመጨረሻም ሲበዛበት ጊዜ ብድግ ብሎ ‹‹እናንተ ሰዎች ለምንድነው እኛን እንደ ኢትዮጵያዊ የማትቆጥሩን?›› አለ በቁጣ፤ ወዳጄ አፍሮ፣ ይቅርታ ጠይቆ፣ ወደነበረበት ወንበር ተመለሰ ‹‹ተፎገርኩ! ሱዳናዊ ወይም ናይጄሪያዊ ወይም ኬንያዊ ይሆናል ብዬ የጠረጠርኩት ሰው- የጋምቤላ ተወላጅ ሆኖ አላገኘው መሰለህ!›› አለኝ፡፡
ብዙዎቻችን እንዲህ ነን፡፡ አናያቸውም፣ አንለያቸውም፣ በእንግዳ ዓይን ነው የምንቀርባቸው፤ የዚህች ሀገር ጉዳይ ግድ የሚሰጣቸው አይመስለንም፤ ስለአኗኗራቸው የጠለቀ እውቀት የለንም፤ ትምህርት ቤት፣ ታክሲ ውስጥና በየመዝናኛ ስፍራው ስናገኛቸው መንፈሳቸው ቶሎ አይዋሃደንም፡፡ ለምን? ምን ሆነን ነው ራሳችንን ያጠበብነው?!
ከጥቂት ወራት በፊት፤ በፌዴሬሽን ምክር ቤት አስተባባሪነት ከመቶ ሃምሳ የማናንስ የኪነ-ጥበብ ሰዎች የኢትዮ-ሶማሌን ምድር የመርገጥ እድል አገኘን፤ ጉዞው ሳምንት የፈጀ እና ብዙ ነገሮች እንድናገናዝብ ያደረገን አይረሴ መስተንግዶ ነበር የጠበቀን፡፡
የሄድንበት ሰበብ ደግሞ÷ ተወላጆቹ እኛ የኪነ-ጥበብ ሰዎችን ከስሰው ነው፡፡ ለወቀሳ፡፡ ‹አታውቁንም፣ እንደ ኢትዮጵያዊ አትቀበሉንም፣ እኛን አዲሣባ ወይም በሌሎች ከተሞች ስታገኙን ከሞቃዲሾ የመጣን ይመስላችኋል፤ የዚያድባሬ ጉዳይ የሚያሳስበን ይመስላችኋል፤ ታላቋ ሶማሌ እንድትመሰረት እንቅልፍ የምናጣ ይመስላችኋል፤ ኢትዮጵያዊነታችንን ላለመልቀቅ ስለምናደርገው ተጋድሎ አታውቁም፤ በዘፈኖቻችሁ፤ በፊልሞቻችሁና በልቦለዶቻችሁ ውስጥ የለንም፤ እናንተ ውስጥ ቦታ የለንም፤ መሬታችንን ረግጣችሁ አታውቁም፤ አርቃችሁናል› ብለው ነው ማንነታቸውን በጨረፍታም ቢሆን ያስጐበኙን፡፡
እዚያ ሄደን - ያየነውና የሰማነው ልብ የሚነካ ‹ለመገንጠል ያለመፈለግ ተጋድሎ› አሁን የሚነገር አይደለም፤ ወቀሳቸውን ግን ብዙዎቻችን ተቀብለነዋል፤ በጅጅጋው ሶማሌና በሞቃዲሾው ሶማሌ መካከል ስላለው የአመለካከት ልዩነት ብዙዎቻችን ጠንቅቀን አናውቅም፤ በአንድ ሚዛን ነው የምንመዝናቸው፡፡
በተለምዶ እኛ ‹ፈላሻ› የምንላቸው፤ መጤ እንግዶች ናቸው ከውጪ የፈለሱ የምንላቸው፤ እነሱ ግን ‹ፈላሻ› ሲባሉ ደስ የማይላቸው፤ ራሳቸውን ‹ቤተ እስራኤላዊ› ብለው የሚጠሩ፤ እስራኤሎች ደግሞ ‹የኢትዮጵያ አይሁዳውያን› ብለው የሚጠሯቸውን ማኅበረሰቦችንስ እንዴት ነው የምናያቸው?
‹ዛጐል› የሚባል አንድ ልቦለድ መጽሐፍ አለኝ - መሪ ገፀ-ባህርዩ ቤተ-እስራኤላዊ ነው - ከልጅነቱ ጀምሮ ቡዳ - የቡዳ ዘር ተብሎ የተገለለ፣ በሃይማኖቱ የተነሣ - እንደ አናሣ፣ እንደ መጻተኛ፣ እንደ መጤ የተቆጠረ፡፡ እና ራሱን እንዲህ ይገልፀዋል ‹…እንደ ጂፕሲ ነኝ፤ ጂፕሲ መሆን ማለት የመጣበት የማይታወቅና እንኳን ደህና መጣህ የማይባል እንግዳ መሆን ማለት ነው ብሏል አሉ አንድ ምሁር፡፡ ‹ጂፕሲዎች› በየትኛውም ዓለም የተናቁ ናቸው፡፡ ሙዚቃቸውና ዳንሳቸው ብቻ ነው ተወዳጅ፡፡ የሁልጊዜ ስደተኞች ናቸው፡፡ … በጣም የተጠሉ፣ የተገፉ፣ ተረጂነት መለያቸው የሆኑ ህዝቦች ናቸው…›
ምንም እንኳን ገጸ-ባህርዩ ያጋነነውን ያህል ባይሆንም፤ ቤተ-እስራኤላውያን ብዙ መገለል ደርሶባቸዋል፤ አድልዎ ተፈፅሞባቸዋል፤ መንከራተት ዕጣ-ፈንታቸው ሆኗል (ወደፊት ስለእነዚህ ሰዎች ሰፊ ነገር አስነብባችኋለሁ)
ይህ ሁሉ ሀተታ ‹ኢትዮጵያ የሁላችንም አልሆነችም› ለማለት ነው፤ ገፍተንና ገፍትረን አውቀንም ይሁን ሳናውቅ ዳር ያስያዝናቸው ማኅበረሰቦች አሉ ለማለት ነው፡፡
ኢትዮጵያ የሁላችንም ትሁን፤ ኢትዮጵያ ጥቂት ብሄሮች፣ ጥቂት ምሁሮችና ጥቂት ታጋዮች ኮሚቴ መስርተው የሚመሯት አገር አይደለችም፤ እኩል ይዝነብልን፤ ለጥቂቶች ሲዘንብ አይደለም ለተቀረው ማካፋት ያለበት፤ ጥቂቶች ሲጠግቡ አይደለም የተቀሩት እንደ ተመፅዋች ‹ትራፊ› በጀት ሊበጀትላቸው የሚገባው፡፡
አሁንም ያልተቀበልናቸው አሉ - አናሣ ብለን፣ ሳናውቃቸው ቀርተን - መጤ ናቸው ብለን፡፡ እንግዳ ተቀባይ ስለመሆናችን እንናገራለን፤ በመስተንግዶአችንም እንኮራለን፤ ጥሩ ነው እንግዳን መቀበል ስደተኛን ማስጠጋት፡፡ እንግዳ ስንቀበል ግን ቤት ውስጥ ያለውን ዘንግተን፣ ችላ ብለንና ፆም አሳድረን መሆን የለበትም፤ ይህን ካደረግን ግብዝነት ነው፤ በግዕዝ አንድ አባባል አለ ‹ለእመ ሀሎ ርሁበ ውስተ ቤትከ እታውፅእ አፍኣ› የሚል - ‹በቤትህ ወይም በደጃፍህ የተራበ እያለ ምፅዋትህን ወደ ውጪ አታውጣ› ለማለት፡፡
...በቤታችን፣ በደጃችን፣ በጓዳችን፣ በጓሮአችን ስንቶቹ ናቸው ፍቅር ተርበው÷ ክብር ተነፍገው፣ ፍትህ ተጠምተው እየኖሩ ያሉት?

7 አስተያየቶች:

  1. "ደቡብ የአቅጣጫ ስም ነው፤ በደቡብነቴ እኮራለሁ ማለት ምንድነው? " I love this!!!

    ምላሽ ይስጡሰርዝ
  2. That's quite a point. And, hey, it is nicely put. Good job buddy ...

    ምላሽ ይስጡሰርዝ
  3. "ኢትዮጵያ የሁላችንም ትሁን፤ ኢትዮጵያ ጥቂት ብሄሮች፣ ጥቂት ምሁሮችና ጥቂት ታጋዮች ኮሚቴ መስርተው የሚመሯት አገር አይደለችም፤ እኩል ይዝነብልን፤ ለጥቂቶች ሲዘንብ አይደለም ለተቀረው ማካፋት ያለበት፤ ጥቂቶች ሲጠግቡ አይደለም የተቀሩት እንደ ተመፅዋች ‹ትራፊ› በጀት ሊበጀትላቸው የሚገባው፡፡" I like it

    ምላሽ ይስጡሰርዝ
  4. ብሄረሰቦች ቀን ራቁት ማስጨፈርና ከነሱ ጋር ፎቶ መነሳት ለብሄረሰቦች ባህል እውቅና መስጠት ሳይሆን ክቡር በሆነው በሰብአዊ ፍጡሮች ላይ እንደ መቀለድና መዝናናት ነው የሚቆጠረው!!!

    ምላሽ ይስጡሰርዝ
  5. ብሄረሰቦች ቀን ራቁት ማስጨፈርና ከነሱ ጋር ፎቶ መነሳት ለብሄረሰቦች ባህል እውቅና መስጠት ሳይሆን ክቡር በሆነው በሰብአዊ ፍጡሮች ላይ እንደ መቀለድና መዝናናት ነው የሚቆጠረው!!!

    ምላሽ ይስጡሰርዝ
  6. ‹ለእመ ሀሎ ርሁበ ውስተ ቤትከ እታውፅእ አፍኣ› የሚል - ‹በቤትህ ወይም በደጃፍህ የተራበ እያለ ምፅዋትህን ወደ ውጪ አታውጣ›

    ምላሽ ይስጡሰርዝ
  7. ‹ለእመ ሀሎ ርሁበ ውስተ ቤትከ እታውፅእ አፍኣ› የሚል - ‹በቤትህ ወይም በደጃፍህ የተራበ እያለ ምፅዋትህን ወደ ውጪ አታውጣ›

    ምላሽ ይስጡሰርዝ