2013 ሴፕቴምበር 22, እሑድ

‹አንበሳው› ማን ነው፤ ‹አህያውስ› የምን ምሳሌ?

   የታወቀ ነው፤ የተለመደ! በየተረቶቻችንና ሥነ-ቃሎቻችን አንበሳ መሪ ተዋናይ ነው፤ ያለእሱ መድረኩ አይደምቅም፤ ምልልሱ አይሞቅም፤ በተቃራኒው ደግሞ አህያን ረዳት ተዋናይ አድርገን ልንቆጥረው እንችላለን፤ ቢኖር ያገለግላል ባይኖር ደግሞ ብዙም አያጐድል ተብሎ ችላ የሚባል፡፡

ይኼ መጣጥፍ በሕይወት መድረክ ላይ ሁለቱንም ሆነን የመተወን እድል ስለገጠመን ሰዎች ለመተረክ የሚሞክር ነው፤ አንበሳ ሆነን ወይም ተብለን በህይወት ሳለን ስለተፈራን ሞተን ስንገኝ ደግሞ ሐውልት ስለቆመልን ሰዎች፤ አህያ ሆነን ወይም ተብለን በህይወት ሳለን በጫንቃችን ላይ ውርደት በጭንቅላታችን ላይ ስቅየት ስለተፈራረቀብን፤ ሞተን ስንገኝ ደግሞ ለማንም ጥንብ ጐታች ስለምንሰጥ ሰዎች የሚተርክ…
እውነት ነው አንበሳ መሆን ደስ ይላል፤ ‹ሞኣ አንበሳ ዘእምነገደ ይሁዳ…› መባል ደስ ይላል፤ አንበሳ ምሳሌነቱ ከድሮ ጀምሮ ለተወደደ እና ለተከበረ ነገር ነው፤ ኢየሱስም ከይሁዳ ዘር ነው ብለን ዘር ማንዘሩን እንቆጥራለን፤ ከአንበሳው ወገን የሚመደብ! እናም የፊተኞቹ ነገሥታት ‹አንበሳነት ከጥንት ጀምሮ በደማችን የተዋኸደ ነው› ለማለት፤ የተቀደሰውን ነገር ‹ያደግንበት ነው› ለማለት፤ ‹ሞኣ አንበሳ…› ይላሉ፤ መጽሐፍ ቅዱስ በአንድ በኩል አንበሳን እንዲህ ለተባረከ ነገር አሳልፎ ሲሰጠው፤ በሌላ ምዕራፍ ላይ ደግሞ አንበሳን በዲያብሎስ ይመስለዋል፤ በነጣቂ፣ በአስጨናቂ፣ በእንቅልፍና በእረፍት ሰራቂ!
እናም እንዲህ እላለሁ፤ የሀገራችንና የአሕጉራችን ቀደምትና የአሁን መሪዎች ‹አንበሳ›ነን ብለው ራሳቸውን ሲመስሉ የትኛውን ዓይነት አንበሳ ሆነው አግኝተናቸዋል?
…ከቅዱሳት መጽሕፍት ውጪ፤ አንበሳ በየተረቱ ውስጥ ድል አድራጊ ነው፤ አንድም አውሬ እፊቱ ይቆም ዘንድ አይቻለውም፤ ‹ንጉሥ› ነው፤ ቀጪ እና ተቆጪ የለውም፤ ንዴቱ ዛፎቹን ያንቀጠቅጣል፤ ተራሮችን ያርዳል፤ እጁ ውስጥ ከገባን ከመዳፉ ፈልቅቆ የሚወስደን ሃይል ማን ነው?... በርግጥ ይህ ሁሉ ሃይል አንበሳው ስልጣን ላይ እስካለ ነው፤ ስልጣኑ የሚጠናቀቀው ደግሞ የጉብዝና ወራቱና የወራት ዘመኑ ሲያከትም ነው፤ ከዚያ በኋላማ፤ ዝንቦች መጫወቻ ያደርጉታል፡፡

ስለአንበሳ የሚያወሩ መጽሕፍት እንደነገሩን፤ አንበሳ ሃይለኛ ገዢ ነው እንጂ ጠንካራ ሰራተኛ አይደለም፤ እንቅልፋም ነው፤ ከሃያ አራት ሰዓት ውስጥ ከሃያ ሰዓት በላይ የሚሆነውን ለመጋደም ያውለዋል፤ ከእንቅልፍ የሚነቃው ሲርበው ነው፤ ‹አርበኛ›ነቱ በማንም ላይ ነው፤ ከወንዱ አንበሳ ይልቅ ሴቷ የተሻለ በየጫካው ተንጐራዳ የአራዊት ሁሉ ንጉሥ የተሰኘ ባሏን ትንከባከበዋለች፡፡
አንበሳን የማምለክ አባዜ በየጉዳዮቻችን ውስጥ ገንኖ ይታያል፤ የምንወዳቸውና የምንፈራቸው ነገሮች በ‹አንበሳ› ስም እንዲጠሩ እንፈልጋለን፤ የሚያገሱ በሚመስሉ የአንበሳ ሀውልቶች ታጥረን መኖር እንፈልጋለን!
በተቃራኒው ደግሞ፤ አህያን እዩት፤ የውርደት ምልክት ነው፤ አንድም ቦታ ጠላቶቹን ድል ስለማድረጉ የሚተርክ ተረት አጋጥሞኝ አላነበብኩም፤ በተረቱ ውስጥ አህያ ካለ ጭነት ሊኖር እንደሚችል መገመት ትችላላችሁ፤ የሚሸከመው ደግሞ ጭነት ብቻ ቢሆን ባልከፋ፤ ግና ውርደት ናላውን እስኪያዞረው ድረስ ይከተለዋል፤ ጌቶቹ እንኳን፤ በእሱ መኖር ኑሮኣቸውን መምራት የቻሉ ገበሬዎች እንኳን፤ እሱ ባይኖር ኖሮ ምን ይውጣቸው እንደነበር የምስክርነት ቃል ከመስጠት ይልቅ፤ በየቦታው ነገር ማሳመርያ ተረትና ምሳሌ ይፈጥሩበታል፡፡
‹አህያም የለኝ፤ እርግጫም አልፈራ› እያሉ፤ ‹አህያ ሞተች ተብሎ ከጉዞ አይቀርም› እያሉ፤ ‹አህያ ቢረግጥህ መልሰህ ብትረግጠው አህያው አንተ ነህ› እያሉ፤ ‹አህያ ሲግጥ ደብተራ ሲያላግጥ ይሞታል› እያሉ፤ ‹አህያና ፋንዲያ አራዳና ገበያ›› እያሉ፤ ‹አህያ ከመሞቷ መጐተቷ› እያሉ፤ ‹አህያ ፈረሱን አንተ አህያ ብሎ ሰደበው› እያሉ፤ ‹አህያን በአመድ ካህንን በማዕድ› እያሉ… ወዘተርፈ እያሉ!
ተረትና ምሳሌዎችን ሰብስባችሁ ብታዩ፤ የተረትና ምሳሌዎቹ ቀማሪዎች አህያን ለማዋረድ ታጥቀው የተነሱ ነው የሚመስሉት፤ ተራጋጭነቱን፣ ሆዳምነቱን፣ በየዓመዱ ተልከስካሽነቱን የሚናገሩ እንጂ ከፍ ያለ ቦታ እንድንሰጠው የሚያደርጉ አይደሉም፤ ድክመቱንና ባህርዩን እየቆጠርን ነው የበታች መሆኑን ሌሎች እንዲያምኑልን የምናደርገው!
እስኪ የትኛው አህያ ነው ሚናውን የሚናገር ቅፅል ስም የወጣለት? ለበሬው፣ ለፈረሱና ለውሻው ልዩ ልዩ ስም ያኖራል-ባላገር፡፡ እነዚህ የቤት እንስሳት መኩሪያዎቼ ናቸው ይላል፤ በሥራ ሰዓት እንዳይለግሙት አሞካሽቶ የሚጠራበት ስም አለው፤ ለስራ የሚያነሳሱ የሚያተጉ ዜማዎች አለው፤ ያጨደውን እህል በአህያ አስጭኖ ወደ ቤቱ ወይም ወደ ገበያ ሲያመራ ግን ለአህያው ሀዘኔታ የለውም፤ የቁልምጫ ቃል አይመጣለትም፤ ማንቆለጳጰስ አይሆንለትም!
…በየጊዜው፤ አንበሳ ሆኖ በፊታችን የሚያገሳው፤ እየተንጐማለለ በፍርሃት የሚያርደንን እንይ እስኪ፤ እኛው ነን በገዛ ራሳችን ቀለን አቅልለን የተመቻቸንለት፡፡
 አለቃ ታዬ ገ/ማርያም (በምኒልክ ዘመን) የተባሉትንና ያሉትን ታስታውሳላችሁ?
በሃይማኖታዊ ጉዳይ ክስ ቀረበባቸውና፤ ሕዝብ በተሰበሰበበት አደባባይ፤ የወቅቱ ግብፃዊ የሆኑት የኢትዮጵያ ጳጳስ እንዲህ አሏቸው አሉ-በቁጣ ‹አንተ አህያ! ሃይማኖትህ ምንድነው?› እሳቸውም በአንድ የውጪ ዜጋ ክርስትናቸው በመነቀፉ ንዴት ገብቷቸው ነበርና ‹አህያ መባላችን ለምን እንደሆነ ይገባኛል፤ እንደ እናንተ ያሉ ባዕዳንን በመሸከማችን ነው!› ብለው መለሱ!
…እንዳልኳችሁ፤ ብዙዎቻችን አንበሳ ወይም አህያ ሆነን ነው እየኖርን ያለነው፤ አንበሳ ተብለን እየተከበርን እና የንግስና ወንበር እየተለቀቀልን ያለው ያ ቦታ የሚገባን ስለሆነ ብቻ አይደለም፤ በዘራችን፣ በጐሳችን፣ ከተፈራ እና ከተከበረ ቤተሰብ ስለተወለድን፣ በኢኮኖሚ ስለተመነደግን፣ ግዛታችንን የማስጠበቅ አቅማችን ጠንካራ ስለሆነና የተቀረው ሕዝብ አንበሳነታችንን አምኖ እንዲቀበል የማድረግና የማስገደድ ችሎታችን ምጡቅ ስለሆነም ጭምር እንጂ!
ስንቶቹ ናቸው፤ እንደ አንበሳ አግስተው፣ እንደ አንበሳ መንጋጭላቸውን አሳይተው፤ የማይገባቸውን ክብር ከመዳፋችን ነጥቀው የወሰዱ? እነዚህ ‹አንበሶች› ከባለስልጣናት ጋር ‹ተሞዳሙደው›፣ ከከፍተኛ ባለሀብቶች ጋር በሕዝብ ላይ ሴራ ጐንጉነው ባጠራቀሙት ገንዘብ፤ በአዲስ አበባና በሌሎች ከተሞች ሰማይ ጠቀስ ፎቆች ሲያበቅሉ፤ እንዴት? አንልም፤ የሀብታቸው ምንጭ ምን እንደሆነ ይጣራ አንልም፤ እናውቃለን ብንናገር እናልቃለን ብለን አፋችንን ለጉመን እንቀመጣለን፡፡ በኋላ፤ ‹ትንፋሼን ሰብስቤ
ተሰትሬ እንደሙት
ያንን አውሬ ሌሊት
ጨፍኜ አሳለፍኩት› ብሎ ተስፋዬ ድረሴ የገጠመውን ግጥም ለማሰላሰል!
በየመስሪያ ቤቱ እና በየስሪያ ቤቱ ለእነዚህ አንበሶች ብዙ ተረቶችን ለመፍጠር ማን ብሎን? ዱር አድሮ በረሃ ውሎ ከመጣው አንበሳ ጋር ማን ይታገላል ብለን፤ የአሸናፊነትን ሚና ለዚህ ‹አንበሳ› ሰጥተናል፤ የዝንብ መጫወቻ የሚሆንበትን ቀን ከመናፈቅ ውጪ፤ የተሸሸገበትን የሙስና እና የዋልጌነት ደን መንጥረን እርቃኑን ለማስቀረት ብቃት ይጐድለናል፡፡ እንፈራዋለን፣ እናከብረዋለን፣ እንሰግድለታለን፣ ንግስና ካንተ ውጪ ለማንም አይገባም እንለዋለን፤ ይህ ሁሉ የሆነው ግርማ ሞገሱ ስለሚያስፈራ፤ የማይናድ የሚመስል የስም ሀውልት እፊታችን ስላቆመ፤ ትላልቅ ባለስልጣናትን በዙርያው እንደ ዛፍ ተክሎ፤ በየጊዜው እነዚህን ዛፍ አብዝቶ፣ ጫካ ሰርቶ፤ እያየነው ስለሚሰወርብን ነው፡፡
እስኪ አህያ የሆነውን ደሀውን ሕዝብ ደግሞ እዩት፤ ማን እንደ ፍጥረት ቆጥሮት ሀውልት ያቁምለት? ማን ለመታሰቢያ ይሆነው ዘንድ አውቶብሱን በስሙ ይሰይምለት? የተማሩ ሰዎች በሚሰበሰቡበት ቦታ ያለው (አ.አ.ዩ. ስድስት ኪሎ) ስንት ቦታ ነው አንበሳ ሀውልት የቆመለት? ይቁም፤ ቦታው በፊተኛው ዘመን ቤተመንግስት እንደነበረ የሚያመላክት ነው፤ ግና፤ ምናለ አብዛኛው ተማሪ እና መምህር የመጣበትን እንዲያስታውስ፤ ገጠር እያለ፣ እርሻ ቦታም ገበያም እየተመላለሰ ለእሱ ‹እዚህ ደረጃ መድረስ› አስተዋፅኦ ያበረከተውን አህያ ልብ ይለው ዘንድ ቢያንስ አንድ ሀውልት እንዲሰራለት የማያደረግ?
መቸ ነው፤ ለዚህ አህያ ለሆነው ተግቶ አዳሪ ሕዝብ ድካሙን የሚመጥን ዜማ የምናበጅለት?
ሲሆን እንዳየነው፣ አህያ ልጅ ብትወልድ ሸክሟን የሚጋራ ታገኝ እንደሆን ነው’ንጂ የክብሯ መጠን ከፍ አይልም፤ ክብር ያለው ዘር የምታገኘው ከፈረስ ተንቅላ በቅሎ የወለደች እንደሆነ ነው፤ ያኔ የአህያ ልጅ በወርቅ ተሸልማ ተብሎ ይተረታል፤ ልጀ ሲያምርባት የማየት እድል ይገጥማታል፤ አሳዛኙ ነገር ግን በዚህች በቅሎ አማካይነት የልጅ ልጇን ‹መሳም› አትችልም!
…እርግጥ ነው በየቤቱ፣ በየቢሮው፣ በየፓርቲው፣ በየቤተመንግስቱ ‹ሃያ አራት ሰዓት› ሙሉ የሚሰሩ አህዮች አሉ፤ የቤት ሰራተኞቻችን ያለእረፍትና እንቅልፍ ለኛ የኑሮ መደላደል የተቻላቸውን ያህል ይተጋሉ፤ ግና በብዙዎቹ ላይ አንበሳ እንሆንባቸውና፤ በጥቂት ጥፋታቸው ምክንያት መቋቋም የማይችሉትን ስድብና ውርደት በጫንቃቸው ላይ እናኖራለን፤ ድካማቸውን የማይመጥን ወርሃዊ ክፍያ እንፈፅማለን፤ ግና ስማቸውን አቆላምጠን ለመጥራት ይተናነቀናል፤ (አህያ መቸ ቅፅል ስም ኖራት?) በየቢሮው እንደንብ የሚተጉ፣ ለድርጅቱ ፀንቶ መቆም ብዙ ላብ፣ እንባና ደም የሚከፍሉ ግና ወሮታቸው የተዘነጋ አሉ፣ ከእነሱ ይልቅ ስራ አስኪያጆች ብቻቸውን ደምቀው፣ ጐልተውና ‹አንበሶች› ተብለው ይሾሙበታል፤ በየፓርቲውም እንደዚሁ፤ በየቤተመንግስቱም እንደዚሁ- ኢህአዴግ አንበሳ ነኝ እንዲል ወይም አንበሳ ነው እንድንለው እነማን ናቸው እንደ አህያ እየለፉ ያሉት፤ ለድርጅቱ ህልውና ብለው አይሆኑ መሆን እየሆኑ ያሉት እነማን ናቸው? በሆነ ምክንያት ከመጋረጃ በስተጀርባ የተቀመጡ፣ ወድደውም ይሁን ተገደው ተደብቀው ያሉ፣ ከባለሀብቱ ጉቦ የማይቀበሉ፣ ለቤተዘመድ ቀርቶ ለቤተሰብ የሚሆን ጊዜና ገንዘብ የሌላቸው እነማን ናቸው? እነማን ናቸው የቀድሞ ጠ/ሚኒስቴር መለስ ዜናዊ ስልጣን ላይ በመውጣታቸው ወይም ቀድመው ሞተው በክብር በመቀበራቸው ሰበብ ብቻ፤ ዝናቸውና ጉብዝናቸው በቅጡ እንዳይነገር እንቅፋት የገጠማቸውና ለድርጅታቸው ታማኝ፣ አንገት ደፊ፣ ትጉሃን አህዮች?
ያም ሆኖ፤ ሕይወት ማለት እንዲህ ናት፤ አንበሳው ጐልቶ እንዲወጣ እኛ አህያ እንሆናለን፤ ወይም ተብለን እንሰደባለን፤ ሁሉም አንበሳ መሆን አይችልም፤ ግና ‹አህያ› ብንሆንም፤ ተፈጥሮ ደግሞ የዝቅተኝነት ስሜት እንዳይጫወትብን ብላ ነው መሰል፤ ‹አንበሳ› ሆነን የምንተውንባቸውን መድረኮች ትዘረጋልናለች፡፡
ከቤታችን፣ ከቢሮአችን፣ ከሀገራችን ስንወጣ ደግሞ፤ ለሆዳችን የምናድር፣ በየአመዱ የምንልከሰከስ፣ ያለምክንያት የምንራገጥና የምናናፋ መስለን እንታያለን፤ ያሳዝናል አህያ መሆን! ስብሐት ገ/እግዚአብሔር፤ ‹አምስት ስድስት ሰባት› መጽሐፍ ውስጥ ‹አሮጊት› የምትል አንዲት ድንቅ አጭር ልቦለድ አለችው፤ ‹አህያ በጣም ያሳዝነያል› ትላለች እብድ ተደርጋ የተሳለችዋ ገፀ ባህርይ ‹…ሲጮህ ሰምተህ የለ? የሀዘን ጩኸት ነው፤ የሀዘን ቀፎ፤ የሀዘን ጥሩምባ፡፡ እህል ይጫንብያል፤ እንጨት፣ ጥድ፣ ሁሉ ነገር ይጨንብያል፣ ዠርባዬ እስኪቆስል ስድብም ሳቅም ይጫንብያል፡፡ መከላከያ ቀንድ የለይ፣ የሚከራከርልይ የለ በምን ፈረድክብይ? ብሎ እግዚአብሔርን ያማርራል፡፡ ደሞው እውነቱን ነው፡፡ በምን ፈረደበት?› ትላለች፡፡
አህያ መሆን ከባድ ነው፤ አህያ መባል ከባድ ነው፤ የአህያን ውለታ ቸል ማለት አህያው በወሳኝ ሰዓት እንዲለግም ግፊት ማሳደር ነው፤ አህያው እንዲርበው ማድረግ፣ የሚገባውን ክብርና ዳረጐት መንፈግ፣ ከመጋጥ እና ከመራገጥ ውጪ ለውጥ እንደማያመጣ ማሰብ፣ አለቅጥ ጭነት እንዲበዛበት ማድረግ… መቸም ብሎ… ‹ከዘላለም ባርነት የአንድ ቀን ነፃነትን› ለራሱ አውጆ… የውርደት ቀንበሩን አሽቀንጥሮ ጥሎ… ልግመኛ መሆኑ አይቀርም፤ የለገመን አህያ በዱላ ብዛት፣ በስድብና ዘለፋ ማሰራት አይቻልም፤ አህያ ቂመኛ ነው፤ አሳዳጊው ወይም ባለቤቱ ወይም ጌታው የበደለው እንደሆነ አሳቻ ቀንና ቦታ ጠብቆ ምቹ ሁኔታ አሰናድቶ ነው ሸክሙን ይዞ የሚተኛው፤ ‹አንተ ራስህ ያሸከምከኝን ነገር ይዘህ ተራራውን ውጣ፤ አቀበቱን ውረድ፤ ከዚህ በላይ በቃኝ ብሎ!› ‹በአንበሳ ደቦል ከተመሰለው ከይሁዳ ወገን የተወለደው ኢየሱስ እንኳን፤ በሆሳዕና በዓል፤ አክብሮኝ እኔ ላይ ተቀምጧል፤ እሱን መስለህ አስተዳድረኝ ብሎ!
ታሪክ ያስተማረንም ነግር አለ፤ በዘውዱ ስርዓት፤ ቦታ ያልተሰጣቸው ውዳሴ ያልጐረፈላቸው በደማችንና በወዛችን ለዚህች ሀገር የከፈልነው ዋጋ አልተቆጠረልንም ያሉ ‹አህዮች› ናቸው፤ አፄ ኃይለስላሴን የሚያህሉ ‹አንበሳ› ገርስሰው የጣሉት! በደርግ ዘመንም፤ መታሰር፣ መጨቆን፣ መታፈንና መገደል የበዛባቸው ተገፊዎች ናቸው ‹ሕ.ወ.ሓ.ት› የሚል ስም አውጥተው፤ ጫካ ገብተው ‹አህዮች› ብሎ የሚንቃቸውን ‹አንበሳ›ውን ደርግ አሽቀንጥረው የጣሉት፤ ይህንንም የሚጥል ይመጣል፤ ‹እድሜ ልኬን አንበሳ እሆናለሁ፤ ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚተላለፍ አንበሳ የሆነ ፓርቲ አለኝ› ብሎ በየሚዲያው ‹ማግሳት› አዋጪ የማይሆንበት ጊዜ አለ፤ አንበሳው ማርጀቱ፣ ድምፁ መስለሉና ጥርሶቹ መርገፉ አይቀርም፤ ርግጥ ነው ሲናቁና ሲገፉ የነበሩት በአህዮች መካከል ተለይተው አንበሳ ሆነው አብዮት ያፈነዱ፤ ለጭቁን አህዮች መብት ታግለናል ያሉ፤ በመጨረሻው ሰዓት ስልጣን እጃቸው ሲገባ ‹እውነትም ይኼ ሕዝብ አህያ ነው› ብለው የታገሉለትን ሕዝብ ይንቁታል፤ ሸክም ይጭኑበታል፤ ሌላኛው አንበሳ መጥቶ እስኪያ ስብረግጋቸው ድረስ! (እስከዚያው ድረስ ግን ላሉትም ለሚመጡትም መሪዎች፣ የቢሮና የቤት አስተዳዳሪዎች ጭምር) እንዲህ እላለሁ-
‹አንበሶች ሆይ፤ አንበሳ መሆን ሃያልነት ነው፤ ግን እየሰራ ያለውን አህያ አትጨቁኑት፤ በልቦናው ጫንቃ ላይ ከሚችለው በላይ የዕዳ ጭነት አትቆልሉበት፤ አጥፍቶ የተገኘ እንደሆነ ዱላው ጥፋቱን የመጠነ ይሁን፤ ‹ውሻህን ስትመታ በርህን አትዝጋ!› ነውና ነገሩ፤ ዱላው ሲበዛበት ማምለጫ ቀዳዳውን ልታሳጡት አይገባችሁምና ቀዳዳ ካላበጃችሁለት መልሶ እናንተን በመነካከስ ራሱን ለማዳን ይሟሟታልና!.. የምትቀርፁት ፖሊሲ ደሀን እንዳይርበውና እንዳይበርደው የሚያደርግ ይሁን- እንዳይለግም፣ እናንተንም ራሱንም እንዳይበድል-
‹አንበሶች› ሆይ! እስካላችሁ ድረስ የእኛ የ‹አህዮች›ን መብት ጠብቁ፤ እኛ ‹አንበሳ› ስንሆን ሸክም በማብዛት አንበድላችሁምና፤ የሚዘልፏችሁን፣ የሚዘርፏችሁንና የሚጨቁኗችሁን አንዳንድ ክፉ ሰዎችን አንሰድባችሁምና!

3 አስተያየቶች:

  1. ወዳጄ! እነደዚህ ዓይነት ለየት ያሉ ተጨባጭነት ያላቸው አተያዮች ያስደስቱኛል፡፡ የበለጠ ስለጉዳዩ እንዳስብ ያበረቱኛል፡፡ በተዋበ አጻጻፍ ጥሩ አድርገህ አስቀምጠህዋል፡፡
    ምን አልባት ሌላ የጹሑፍ ሥራ ከረዳህ የበለጠ እንድታያው በማሰብ በተለያዩ የሥራ አጋጣሚዎች ወደ ተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች ስዘዋወር ያየሁትን ላጋራህ፡፡ በአብዛኛው የምሄድበት አካባቢ ነዋሪዎችን አህያ አያያዝ በማየት ሥለእነርሱ አስተሳሰብ ለመገመት ፍንጭ ማግኛ አድርጊ እወስደዋለሁ፡፡ ምንአልባት ትክክል አልሆን ይሆና፡፡ የአካባቢዎቹን ስም ሳልጠቅስ አንዳንድ ቦታ ለአህያ ጥሩ ክብርና አያያዝ አላቸው፡፡ ከአቅም በላይ አይጭኗቸውም፡፡ አይደበድቧቸውም፡፡ ሌላኛው አካባቢ ያየሁት ግን ከዚህ በጣም የተለየ ነው፡፡ ከአቅም በላይ ጭነት ያበዙቧቸዋል፡፡ እላያቸው ላይ ዘለው ይወጣሉ ይወርዳሉ፡፡ ይረግጧቸዋል፡፡ ሌላም ሌላም ተገቢ ያልሆነ ነገር ሲያደርጓው ማስተዋል ችያለሁ፡፡

    ምላሽ ይስጡሰርዝ
  2. እንዳለ ጌታ፣ ቅዱሱ መጽሐፍ፡ "...ቃልም በጊዜው ምንኛ መልካም ነው!" ደግሞም፡ "የወርቅ እንኮይ በብር ፃሕል ላይ፤ የጊዜው ቃል እንዲሁ ነው።" እንደሚል(ምሳሌ ፩፭፣፪፫፤ ፪፭፣፩፩፣) ሰናይ መልዕክት ያዘሉ የጊዜውን ጹፎች ታስነብበናለህና፣ አንዱ ጌታ ሰላም፣ እድሜና ጤና ይስጥልን!

    ምላሽ ይስጡሰርዝ