2013 ኦገስት 24, ቅዳሜ

ሰው ለሰው


አስናቀ- ‹ተወዳጁ› ሰይጣን

አበበ ባልቻ (አርቲስት) ‹ሰው ለሰው› የተሰኘውን ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማ ዝነኛ እንዲሆን አድርጐታል ብዬ አምናለሁ፤ ‹ሰው ለሰው› ድራማ  ከፍ ያለቦታ እንዲሰጠው አበበ ባልቻ ትልቅ ሚና ተጫውቷል ብዬም አምናለሁ፤ ረቡዕ በመጣ ቁጥር፤ መጥቶም በመሸ ቁጥር ሰዎች ማወቅ ከሚያጓጓቸው ነገሮች መካከል አንዱ ‹አስናቀ እንዴት እንደሰነበተ› መረጃ መለዋወጥ ሆኗል!
‹ሰው ለሰው› ውስጥ ያሉ ገጸ-ባህርያትና ድራማውን በመድረስ፣ በማዘጋጀት፣ በመተወንና ሙያዊ ድጋፍ በማድረግ እየተባበሩ ያሉ ሙያተኞች ስማቸውን በልባችን ውስጥ ማስፃፍ ችለዋል፤ በክብር እንግድነት የሚፈለጉባቸው መድረኮችም ጨምረዋል፤ በአጠቃላይ የ‹ሰው ለሰው›› ሰዎች የብዙዎቻችን ቤተኞች ሆነዋል፡፡ ይኼ መታደል ነው!! ግና ደራሲዎቹ (በተለይ ሰለሞን ዓለሙና መስፍን ጌታቸው) በየመጽሔቱ ስለዚህ ተከታታይ ድራማ በሚሰጡት ቃለ መጠይቅ ተባብሮ፣ ተከባብሮና የሚያጋጥሙ ችግሮችን በብልሃት እንዴት እንደሚወጡት ብናነብላቸውም፤ ድራማው ሊጠናቀቅ እየተቃረበ መሆኑንና ከዓመት በላይ እንደማይቆይ የሰጡትን መረጃ ልብ ብንለውም፤ እንደ ቴሌቪዥን ድራማው ተከታታዮች፤ እኔንና ጓደኞቼን ሲያሳስቡ የቆዩ ሶስት ነጥቦች አሉ፤ እነዚህ ነጥቦች ከወዲሁ ማረሚያ ካልተበጀላቸው፤ ማቃኛ ካልተደረገባቸው አንዳንድ ተመልካቾችን ድንዛዜ ውስጥ ሊከቱ ይችላሉ የሚል እምነት አለኝ፡፡
‹ሰው ለሰው› ውስጥ ያሉ ገጸ-ባህሪያትን ወክለው በመጫወት ብዙዎቹ የሚደነቁ ቢሆንም፤ ገጸ ባህርያቱን በመፍጠር በኩል ግን ደራሲዎች ልብ ያላሏቸው ወይም ችላ ብለው የናቋቸው ወይም በማጠቃለያ ክፍሉ ትኩረት ሰጥተን እንመለስባቸዋለን ብለው እስካሁን በቅጡ ሲዳስሷቸው ያላየናቸው ነጥቦች አሉ፤ እነሱም አንድ በድራማው ውስጥ ሴቶችን ደካማ አድርጐ መሳል፤ ሁለት፣ ተመልካቹ እንደ አርአያ የሚወስዳቸው ቤተሰቦች አለመኖር፤ ሦስት፣ ‹ሰይጣን› የሆነውን ገጸባህርይ አጀግኖ አሳዳጅ ፖሊሱን አኮስምኖ የማቅረብ ሁኔታ…
በ‹ሰው ለሰው› ድራማ ውስጥ ያሉ ሴት ገፀ-ባህርያትን ልብ ብዬ እንዳያቸው ያደረገኝ ወዳጄ ዳዊት ንጉሱ ረታ ነው፤ ‹ሴቶቹን እዩዋቸው፤ ወጣቶቹም በእድሜ የገፉትም በቸገራቸው ጊዜ መፍትሄ ከማመንጨት ይልቅ መደናበርና መደናገር ይታይባቸዋል፤ በቀላሉ ተሸናፊዎች ናቸው፤ ምንዱባን! ለሀዘናቸው መጠጊያና መጠለያ እንዲሆን የሚመርጡት ወንድን ነው፡፡
አይጠይቁም፣ አይራቀቁም፣ በወሬ ይሰበራሉ፤ ወንዶችን ያምናሉ፤ በቀላሉ ለፍቅር ይንበረከካሉ፤ በቀላሉ በስጦታ ይደለላሉ፤ በቀላሉ የንዋይ ሎሌ ይሆናሉ፤ በቀላሉ ቀላል ይሆናሉ- ተመሳሳይነት ይታይባቸዋል፤ ይሄ የደራሲዎቹ ችግር ነው፤ አብዛኞቹን ሴት ገጸ-ባህርያት ለምንድነው አንድን ነገር በጥልቀት ከመመርመር ይልቅ፤ ድንገት ወደ ህይወታቸው ጠልቆና ዘልቆ የገባ ወንድ ወደፈለገበት አቅጣጫ የሚያሽከረክራቸው?›
…ሌላው የሚያሳስበን የገጸ-ባህርያቱ ቤተሰባዊ ህይወት ነው፤ ‹ሰው ለሰው› የተለያዩ ቤተሰቦች ከልጆቻቸው ጋር የሚያጋጥሟቸውን ፈተናዎች ለማሳየት የተመቻቸ ነው፤ ደራሲዎቹም ይህንን ለማዋቀር በብዙ እንደደከሙበት ያስታውቃል፤ ድርሰቱ ብዙ ቤት ገብቶ ይወጣል! ይህ ብዙ ጉድ አይቶ የመውጣቱ ነገር ይበል የሚያሰኝ ቢሆንም፤ በቤተሰቦቹ በኩል የሚነገሩን እውነቶች ግን ድካም ይታይባቸዋል፡፡
በ‹ሰው ለሰው› ውስጥ ያሉ ቤተሰቦች ‹አብሬያቸው በኖርኩ!› የሚያስብሉ አይደሉም፤ እያንዳንዱ ቤት ውስጥ ጋጠ-ወጦች አሉ፤ ተበደልኩ ባይ አኩራፊዎች አሉ፤ ተስማምተው በፍቅር ከመኖር ይልቅ ወደ እርቅ የሚወስደውን መንገድ ከመያዝ ይልቅ፤ ወጣት ገፀ-ባህርያቱ ወላጆቻቸውን የሚያንጓጥጡ ይሆናሉ፤ አፈንግጠው የሚወጡ ይሆናሉ- ደራሲዎቹ በአንድ ወጣት ላይ አንድ ችግር ሲከሰት ወጣቱ ችግሩን ለማስወገድ የመረጠው ሀሳብ ተቀባይነት ሳያገኝ ሲቀር ሻንጣ አንጠልጥሎ መውጣት ወይም አገር ለቅቆ መጥፋትን መፍትሄ ያደርጉታል፡፡ በድራማው ውስጥ አንድ ገፀ-ባህርይ እንዲህ ያደርግ ይሆናል፤ ሁሉም ወጣቶች ከቤታቸው ራሳቸውን አባርረው ለወላጆች ጭንቀት መንስኤ የሚሆኑበት ምክንያት ግን አይታየንም፤ እንዴት እንዲህ ተወዳጅ በሆነ-አእምሮን ሰቅዞ በሚይዝ ተከታታይ ድራማ- እንደ ‹አርአያ› የሚቆጠር ግለሰብ ወይም ቤተሰብ ይጠፋዋል? የሚል ጥያቄ ተወልዶብናል፡፡ (ባርችን፣ የመዲን፣ የሶስናን፣ የፍሬዘር እህትን፣ የአስናቀን ልጅ ልብ ይሏል?)
ሶስተኛው ነጥብ የአስናቀ ጉዳይ ነው፤ ስጀምር እንደተናገርኩት ‹ሰው ለሰው› ያለ አስናቀ ንብ የሌለው ቀፎ ነው፡፡
አበበ ባልቻ ወክሎት የሚጫወተውን ገጸ-ባህርይ መጀመሪያ ዝናህ ብዙ እንዲጫወተው ታጭቶ እንደነበረ፤ ዝንናህ ብዙ ኢቲቪ ባደረገለት ቃለ መጠይቅ ገልጾ ነበር፤ ‹…ክፉ ገፀ-ባህርይ ወክዬ መጫወት ስለማልፈልግ ተውኩት! ነበር› ያለው፤ መልሱ አስቂኝ ነበር፤ አንድ አርቲስት ለትወና ሲፈለግ እኩይና ሰናይ ገፀ-ባህርያትን አማርጦ ከሰራ ምኑን የሙያው ቤተሰብ ሆነ?
የሆነው ሆኖ፤ አበበ ባልቻ ‹አስናቀ›ን ተረከበው፤ እንኳንም ተረከበው!
…አስናቀ የድራማው ምሰሶ ነው፤ ምሰሶው ከወደቀ ድራማው የታነፀበት ቤት ይደረመሳል፤ ራሱን ችሎ መቆም አይችልም፤ እስካሁን እንዳየነው አስናቀ ብርቱ የተባሉትን በክንዶቹ ይዞ፣ ሃይለኞችን በመዳፉ ጨፍልቆ ‹ነብር አየኝ በል› የሚያስብል ነው፡፡
አበበ ባልቻ በየሄደበት የክብር ወንበር እንዲለቀቅለት ያደረገ፣ በየደረሰበት ወፍራም ጭብጨባና ሞቅ ያለ ፈገግታ እንዲቸረው ያደረገ ይኼ አስናቀ የተባለው ገፀ-ባህርይ፤ አሁን አሁን ግን ያሳስበን ጀምሯል፡፡
ክፉ ገፀ-ባህርይ በዚህ ልክ መወደዱ አይደለም ያሳሰበን፤ ለምን ኢያጐን ወክሎ እንደተጫወተው ገጸ-ባህርይ ለምን መድረክ ላይ ጫማ አልተወረወረበትም፤ ለምን ሽጉጥ አልተተኮሰበትም? ማለታችንም አይደለም-
ደራሲዎቹ ገፀባህርዩን ሲቀርፁ ‹የቆጡን አወርድ ብለው የብብታቸውን እየጣሉ ነው›፤ ተወዳጅ የሆነ ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማ መጻፋቸውንና ለተመልካች አሽሞንሙነው ማቅረባቸውን እንጂ በታዳሚው ህሊና ውስጥ፤ በተለይ በታናናሾቻችን ልቦና ውስጥ የተሳሳተ መልዕክት ማስቀመጣቸውን ልብ ያሉት አይመስልም፡፡ በአስናቀ ውስጥ ራሳቸውን እየፈለጉ ያሉ፣ እሱን መስለው መኖር የሚመርጡ፣ በአቋራጭ የመክበርን ጥበብ የሚኮርጁ- ገንዘብ ሊገዛው የማይችል ነገር እንደሌለ የሚያምኑ፣ ወንጀል ቢሰራ እንኳን ገንዘብ ካለው፣ ሃይል ካለው አንድም መርማሪ ፖሊስ አሳድዶ እንደማይዘው ይሰማው የጀመረ ተመልካች እየበዛ ነው፡፡
አስናቀን ወደን ፈለጉን ለመከተል ታዳሚ እንድንሆን አስበው ደራሲዎቹ እንዳልጻፉት አምናለሁ፤ ገፀ-ባህርይው ከቁጥጥራቸው ውጪ እየሆነ እና አሸናፊ እየሆነ እየፈተናቸው ያለ ይመስለኛል-
በሚዲያው እንዲህ አይነት ነገር መነገር አለበት ብለን አናምንም፤ ታናናሾቻችሁን ጠይቁ፤ በድራማው ውስጥ አስናቀ ነው ተፅዕኖ አሳዳሪ፤ አስናቀ ነው የሚያስቀና ኑሮ እየኖረ ያለው፡፡
ይህን አይቶ ያደገ ሰው፤ ሃይለኝነትን፣ ሌብነትን፣ አማጋጭነትን፣ መሰሪነትን፣ በአቋራጭ መክበርን፣ በገንዘብ ብዛት ሰው መግዛትን ከአስናቀ የተማረ ሰው ነገ ለቁጥጥር አይቸግርም ወይ? እንላለን፤ አይደለም እንዲህ ስጋ ለብሶ ነፍስ ዘርቶ በየሳምንቱ ቤታችን የገባ ገፀ-ባህርይ ይቅርና በተረትና በታሪክ ውስጥ የምናገኛቸው ባለታሪኮች ታናናሾቻችንንም እኩዮቻችንንም የመቅረጽ አቅም አላቸው፤ በተሳሳተ መንገድ ገፀባህርይውን የሚኮርጁት እንዳይኖሩ፤ የአስናቀ የሚያስጐመጅና የማን ያዘኛል ኑሮ፣ ትኩረት ሊደረግበት ይገባል- መርማሪው ፖሊስ ምን እያደረገ ነው? እስከመቼ ድረስ ነው የሚያባርር ግን ወንጀለኛን የማይይዝ ባለሞያ ተደርጐ የሚተረበው? የፍሬዘርን ታላቅነት፣ አርቆ አስተዋይነት፣ እንደ አስናቀ ያለብርቱ ጨካኝን በቁጥጥር ስር ሲያውለው የምናየው መቼ ነው? ቀኑ አልራቀም? (ኖህ የሚባል አንድ ታዳጊ ልጅ አለ፤ መዋዕለ ህፃናት ሄዶ ከእኩያው ተጣልቶ መጣ፤ ተሸንፎ ተደብድቦ ነው የገባው - ምንሆንክ? ልጄን ምናን አገኘብኝ አለች ደንግጣ፤ ልጇን ይዛ ወደመዋዕ ለህፃናቱ ገባች፤ የደበደበኝ አስናቀ ነው አለ ለዳይሬክተሩ፤ የሚገርመው አስናቀ ግቢው ውስጥ ዝነኛ ነው፤ በአጃቢ ነው የሚንቀሳቀሰው፤ የማንንም ዕቃ ነጥቆ ቢወስድ የሚገዳደረው የለም፤ እኔ የሰው ለሰው አስናቀ ነኝ ብሏቸዋል- መጠሪያ ስሙን ቀይሮ፡፡ ይህ ታዳጊ ልጅ አቀማመጡም አነጋገሩም እንደ አስናቀ ነው…)
ደራሲዎቹ ‹ሳቢዶ ሜቶዶሎጂ› በተባለው የአፃፃፍ ስልት፤ ታሪካቸውን እያዋቀሩ፣ ገፀ-ባህርያቱን እየቀረፁ ያለ ይመስለኛል፤ የአፃፃፍ ስልቱ በሌላው ዓለምም የተለመደ ነው፤ እንደ አቤል ቅን፣ ታዛዥና ንፁህ የሆነ አንድ ሰው፤ በተቃራኒው ደግሞ እንደ ቃኤል ቀናተኛና እምቢተኛ የሆነ ሌላ ገፀባህርይ፤ ክፉም ደግም ያልሆነ ሌላ ገፀ-ባህርይ ተቀርፆ፤ እነዚህን ምሰሶ አድርጐ ረብ ያለው ጭብጥ ማስተላለፍ አንዱ መለያው ነው፡፡ በዚህ የአፃፃፍ መንገድ ፓፑሌሽን ሚዲያ ሴንተር ‹የቀን ቅኝት›ና ሌሎች ተከታታይ የሬዲዮ ድራማዎችን አቅርቧል፤ ከደራሲዎቹ አንዱ መስፍን ጌታቸው ነበር፡፡
መስፍንም ሆነ ሰለሞን ከዚህ ቀደም ለህዝብ ባቀረቧቸው ፊልሞች (ዙምራንና አንድ እድልን ልብ ይሏል) ማስተላለፍ የፈለጓቸው መልእክቶች ማለፊያ ነበሩ፡፡
እዚህ ‹ሰው ለሰው› በተሰኘው ድራማቸው ውስጥ ግን ምንም ሳይሉ፣ ምንም ሳይናገሩበትና አንዳች መልእክት ሳያስተላልፉበት ድራማው እንዳይጠናቀቅ እሰጋለሁ፤ እስካሁን ድረስ ደራሲዎቹ የተመልካችን ቀልብ የመግዛት አቅማቸውን አሳይተውበታል፤ መሰልቸትን ለማስወገድ የተለያዩ ዘዴዎችን ቀይሰዋል፤ ገነት ንጋቱ ወክላ የምትጫወተው ገፀ-ባህርይ የተጋነነ እና ከአንዲት ኢትዮጵያዊት እናት የማይጠበቅቅ ቢሆንም፣ የት እንደገቡ ያልታወቁና ድንገት ብቅ ብለው ስቀው ወይም አስለቅሰው በእንጭጩ የሚቀጩ ቤተሰቦች ታሪካቸው ተድበስብሶ ቢያልፍም፤ ከንፁሃንና ከትጉሃን ይልቅ መሰሪዎች በተደላደለ ሁኔታ በምቹ ፍራሽ ሲንፈላሰሱ ብናይም፤ ሴቶቹ አልቃሾችና ተልከስካሾች ተደርገው ቢቀረፁም፤ ምነው እሱን ባደረገኝ፣ የእነሱ ባደረገኝ የሚያስብሉ መንፈሳዊ ቅናት የሚያሳድሩ ጠንካራና በቀላሉ ወድቀው የማይሰበሩ፤ ቢሰበሩም በጽናት ታግለው የሚያሸንፉ ግለሰቦችና ቤተሰቦች ቢጐድሉትም፤ አዝናኝና እውቀት ከማቀበልና መረጃ ከመስጠት ይልቅ ልብ-ሰቃይ ታሪክ በመፍጠር ግን የታወቀና የተደነቀ ነው፤ መቼ መጥተው ጉዳቸውን ባየነው የሚያስብል፡፡
የአስናቀ ጉዳይ ግን ከወዲሁ ቢታሰብበት አይከፋም፡፡
እነዚህ ጥቂት ምሳሌዎች ናቸው፤ በጥንቃቄ የተቀረፁ ደጋግም ሆነ ክፉ ገፀ-ባህርያት በአንባብያን ላይ የሚያጠሉት ጥላ ቀላል አይደለም፤ የጀርመናዊውን ጐቴ (1749-1832) "The sorrows of young werther" የተባለውን መጽሐፍ ያነበቡ ብዙ ወጣቶች ራሳቸውን ገድለዋል፡፡ በዚህ ስለፍቅር በሚተርከው ልቦለድ ላይ ያለው ገፀባህርይ በታሪኩ መጠናቀቂያ ላይ ራሱን ያጠፋል፤ ይህን ያነበቡና የወጣቱ ውሳኔ ልክ ነው ያሉ- ጥቂት አንባብያን እጃቸውን በእጃቸው በልተዋል፡፡
…መስፍን ሃብቱ የሚባል አንድ ኢትዮጵያዊም ነበር- በ1960ዎቹ መጀመሪያ በባዕድ ሀገር ራሱን ያጠፋ፤ ይህ በአሜሪካ አገር የተማሪዎችን ንቅናቄ በመምራትና ፓርቲ በማደራጀት የሚታወቅ ወጣት፤ ራሱን ለማጥፋት ያበቃውን ‹ፀፀት› ለጊዜው እንተወውና ከመሞቱ በፊት ግን አንድ ፊልም እያየ ነበር- ፊልሙ ስለ አንድ ታዋቂ የደች ሰዓሊ (ቫንጐህ ነው ሰውየው) ይተርካል፣ ፊልሙ ሊጠናቀቅ ሲል ይህ ታላቅ ሰዓሊ ራሱን ያጠፋል፤ መስፍን ይህንን ፊልም አየ፤ ቤቱ ገባ፤ በሰራው ፖለቲካዊ ስህተት እጅጉን ተፀፅቶ፤ በጓደኞቹ ዘንድ በደረሰበት መገለል ክፉኛ ተጐድቶ ነበርና፤ ለመጽናናት ብሎ ከከፈተው ፊልም አንዳች ነገር ወሰደ፤ መፍትሄ አገኘ፤ እንደ ፊልሙ ባለታሪክ- በሰው ሃገር ራሱን ገደለ፡፡
እንደ ኢትዮጵያ ባሉ-ድህነት ቀፍድዶ በያዛቸው ሀገራት ይቅርና በሰለጠኑት ዓለማትም ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማዎች ሳናውቀው በልባችን ውስጥ ከባድ ማኅተም ያሳርፋሉ፤ በአመለካከታችን ላይ ተፅዕኖ ያሳድራሉ፤ የተንኮልን ተክል ወይም የደግነትን አበባ ይዘራሉ፤ እቤታችን አስገብተን በፈቃደኝነት እንማርላቸዋለን ለዚህም ነው ከልቦለድም ከቴአትርም በላይ ተከታታይ ድራማዎች አስተውሎትን የሚጠይቁት፡፡ ትልቁም ትንሹም እኩል የሚከታተለው ነውና፤ ምሁሩም መሐይሙም በአንድ የመዝናኛ ገበታ እንዲታደሙ የሚያደርግ ነውና!
…ከመርፈዱ በፊት መንቃት ያስፈልጋል ለማለት ነው ይሄ ሁሉ፤ አስበውበት ከሆነ እሰየው፤ ካላሰቡበት ደግሞ እንዳይዘናጉ ለማስታወስ ነው…
…‹አርአያ› እንዳናጣ፣ ከራሳችን እንዳንጣላ፣ ራሳችንን እንዳናጠፋ፣ ሰብዕናችንን እንዳናቆሽሽና በተሳሳተ መንገድ እንዳንማርና እንዳናስተምር ለእናንተም፣ ለእኔም ለመሰሎቻችንም የተፃፈ ማስታወሻ ነው - ይሄ፡፡
ከአክብሮት ጋር፡፡

2 አስተያየቶች: