2013 ሴፕቴምበር 3, ማክሰኞ

ከጥቁር ሰማይ ስር



ጥዋት ጥዋት፣ ወደ ቢሮ ለመሄድ - መታጠፊያው ጋ ሲደርስ - እተለመደ ቦታዋ ቁጭ ብላ የሚያጉተመትም በሚመስል ድምጿ ያለማቋረጥ ስታወራ ይሰማታል፡፡ የአራት ልጆች እናት የሆነችዋን የኔ ቢጤ፡፡
የእናታቸውን ያህል ባይሆንም ጎስቁለዋል፡፡ እንደ ምጣድ ማሰሻ የቀድሞ ከለሩ ያልታወቀ ከነቴራ ለብሰዋል - ከወገባቸው በላይ፡፡ ከመሃከላቸው አንዳቸውም ቃጭል አንጠልጥለው አልተወለዱም፡፡
. . . በማያውቀው ቋንቋ ታወራቸዋለች፡፡
ልጆቿ አይመልሱላትም፡፡ እርስ በርሳቸው ሲጨዋወቱ በአዲስ አበባ አማርኛ ነው የሚግባቡት፡፡
እንዲህ በከንቱ ጉንጭዋን የምታለፋው በውስጡ ያደረውን ጩዋሂ መንፈስ ላለማዳመጥ ይሆን? ብሎ ያስባል
ጤንነቷን የማይጠራጠር የለም፡፡ አንዳንዶች ፥ ስለ ልጆቿ የወደፊት ዕጣ ፈንታ ማሰላሰል ስታበዛ ይሆን ያተሳሰብ ማዛንዋ የተዛባው? ይላሉ፡፡
ሁልጊዜ ያልተለመደ ነገር ስታደርግ ያጋጥመዋል፡፡ እጇ ላይ የተገኘን ማንኛውም ነገር ለአራት አካፋፍላ ለልጆች ታድላቸዋለች፡፡ ለራሷ የምታደርገው አይኖራትም፡፡ ከሲታ ናት ደግሞ፤ ያለ እህል ውሃ ለመኖር ሙከራ የጀመረች እስኪመስል ድረስ፡፡
ሳንቲም ተወርውሮ እግሯ ስር ያረፈ እንደሆነ ቅጭልጭልታውን ሰምታ እንኳን ቀና አትልም፡፡ ማንንም አይታይም - አገጯን ጉልበቷ ስር ደብቃ ነው፤ ቀኑን ውላ የምታመሸው፤ የምታነጋውም! መንገድ ዳር፡፡
እሷ ካለችበት ፈንጠር ብሎ - አንድ ክፉ የማይመስል - ዘባተሎ ለባሽ ጎልማሳ - በጠባቂነት መንፈስ ዓይኑን ያንከራትትባቸዋል፡፡ በየመንገዱ የሰበሰባቸው ቁርጥራጭ ሲጋራዎች ከኪሱ እያወጣ ያጨሳል፡፡
የልጆቿ አባት ይሆን? . . . ወይስ ወደ ጎዳና ከወጣች በኋላ የተወዳጃት ጊዜያዊ ባል?! . . . ወይስ ከክፉ ሊታደጋት ተከትሏት የመጣ . . . ? ወይስ ለነፍሱ ያደረና እነዚህን ሕጻናት ታድጎ በቅዱሳን መዝገብ ስሙን ለማስጻፍ የሚተጋ ይሆን?
ከሁላቸውም የምታንሰዋ ሕጻን ዕለተሞቷ የተቃረበ ገመምተኛ ነው የምትመስል፡፡ ሁለት ዓመት ይሆናታል፡፡ የምትተልቀዋ ስድስት እንቁጣጣሾች አክብራለች፡፡ ከእናቷ ጎን ፈቀቅ ሳትል ወጭ ወራጁን ታጤናለች፡፡ ከአጠገቧ አንድ ሰው ያለፈ እንደሆነ ‘ጋሽዬ ለዳቦ?’ ብላ ተለሳልሳ ትለምናለች፡፡
የተሰጣትን አጠራቅማ ሃምሳ ሳንቲም ሲሞላ ዳቦ ለመግዛት ሩጫዋን ታቀጥነዋለች፡፡ ታናናሾቿም ከተደበቀችበት ክንፍ አፈትልካ እንደምትወጣ ጫጩት ከእናታቸው ጉያ ሾልከው ይከተሉዋታል፡፡
የገዛችውን ዳቦ እናቷ እጅ ላይ ታኖረዋለች፡፡ እናት ዳቦውን ለአራት ታካፍለዋለች፡፡ ለራሷ የምታስቀረው የላትም፡፡
ልጆቿም እንድትበላላቸው አያባብሏትም፡፡
አንዳንዴ፣ ስለ እናታቸው ምን ያስቡ ይሆን? ብሎ ያስባል፡፡ ሳይሳለማቸውና ድምጹን ሳያስደምጣቸው ማደር አይሆንለትም፣ አንጀቱ እየተንሰፈሰፈ በደስታ ይጨብጣቸዋል፡፡ እጁን ለመንካት ይሩዋሩዋጣሉ - እየተጩወጩዋሁ፡፡
እናትየው ይህን ሁሉ አታይም፡፡ ቀና ብሎ የው ዓይን ማየት የሚሆንላት አይመስልም፡፡ ብታያቸው ለመደሰቷ ምክንያት መሆን ቢችል ደስ ይለዋል፡፡
ፊገግታ ፊቷ ላይ ሲጫወት ምን እንደሚመስል ማየት ያልፈለገበት ጊዜ ይኖር ይሆን?
ማታ፡፡
ሳንቲም ፍለጋ ኪሶቹን ደባበሰ፡፡ ድፍን አምስት ብር ተገኝታለች፡፡ ዙሪያውን ቃኘ፡፡ ያልተዘጉ ሱቆች አይታዩም፡፡ የት ይዘርዝረው?
ለአራት ተዘጋጅታ የነበረች ብር ናት፡፡ ምሳ ሳይበላ ነው የዋለው፡፡ ሳይበላ ስለዋለ ነው መሰል ከተራራ ላይ እየተንከባለለ እንደሚወርድ በርሜል ሆዱ ሲያጉረመርም ይሰማዋል፡፡ ብሩን የት ይዘርዝረው?
የተቻኮሉ መገደኞች በጥርጣሬ እያስተዋሉት ይተላለፋሉ፡፡ ግን ማንንም ‘ዝርዝር ከያዛችሁ ተቸገሩልኝ’ ብሎ መጠየቅን አልፈለገም፡፡
“ምሳና እራት ሳልበላ ብቀር ምን ይጎድልብኛል?” ብሎ ሆዱን ሲደልል ቆየና አምስት ብሩን አወጣ፡፡ አወጣና ሌላ ጊዜ እንደሚያደርገው አጠገባቸው ጣል አድርጎ ‘ደህና እደሩ’ ማለቱን ብቻ አልፈለገውም፡፡
አምስት ብሩን በእናትየው መዳፍ ላይ አኖረው፡፡
ፈገግታ አላሳየችውም፡፡
አላየችውምም፡፡ ድምጿም አልተደመጠ፡፡
ትልቋ ልጅ ብቻ ናት - በእጃቸው ትልቅ ነገር እንደገባ የገባት፡፡ እንደመፈንደቅም እንደመደንገጥም ብላ የተኙትን ቀሰቀሰቻቸው፡፡ ለማንቃት አልተቸገረችም፡፡ ጠባቂያቸውን ግን ተወችው፡፡ ስጋውን ለእንቅልፍ አሳልፎ ሰጥቷል፡፡
አቀማመጣቸውን ልብ ብሎ ላየ እናትየው እንስራ ትመስላለች፡፡ ሕጻናቶቿ ደግሞ እንስራው ተንሸራትቶ እንዳይሰበር ደግፈው የያዙት ጠጠሮች! . . .
እናትየው እጇ ላይ የገባውን አምስት ብር ለሁለት ከፈለችው፡፡ የከፈለቻቸውን የብር ክፍልፋዮች በሚያስገርም ፍጥነት እንደገና ቀዳደደቻቸው፡፡ ሁለት ሶስት ባልሞላ ደቂቃ ውስጥ ለልጆቿ አከፋፈለቻቸው፡፡
ትልቅዬዋ ለምቦጭዋን ጥላ በእጇ የነበረውን ሳንቲም እናቷ እናት ላይ በተነችው፡፡ “ብዙ ዳቦ የሚገዛ፣ ሁልጊዜ እንዳይርበን የሚያደርግ፣ ብር ነው ኮ እንደዚያ የማይጠቅም ያደረግሽው!” አለቻት ሳግ እየናነቃት፡፡
እናት የተባለችው ያልገባት ይመስል ልጇ ላይ አተኮረችባት፡፡ መፅዋቹም ትርጉሙን ባልተረዳችው አተያይ ሲያያት አገኘችው፡፡
እንደተያዩ ቆዩ፡፡ ትናንሽ ዓይኖቹ እንባን ያዘንቡ ጀመር፡፡ እንባው እየንሸራተተ - በጠይም ፊቱ ላይ መስመር እያበጀ - ወደ አፉ ደረሰ፡፡
ይሄ ሲሆን አምስት ብሩን የሸረካከተችው እናት ልብ ብላ አየችው፡፡
መፅዋቹ መንቀሳቀስ ጀመረ፡፡
የሚንቀሳቀስ ጥላ መስሎ በዝግታ እየተጓዘ ወደ ጨለማው ሆድ ውስጥ ገባ፡፡
ቅርፁ እስኪርት ድረስ በዓይኗ ሸኘችው፡፡
ከዚያስ በኋላ . . .
ሌቱን በሙሉ - በታላቅ ምሬት - ባለተለመደ አጩዋጩዋህ ስትንሰቀሰቅ አደረች፡፡ አምስት ብሩን

ያለ አገልግሎት
ስላስቀረችው ሊሆን ይችላል፡፡ ያቺ ብር ርሃቧን ልታስወግድበት ትችል እንደነበር ተገንዝባ ይሆናል፡፡ ወይም የዚያን መፅዋች እንባ ስታይ አንድ ነገር እንዲታወሳት ምክንያት ሆኖ ይሆናል፡፡
ለምን እንዲህ እንዳደረገች
የጠየቃት አልነበረም

4 አስተያየቶች:

  1. የሰው ልቡ የወፍ ወንዱ አይታወቅ አይደል

    ምላሽ ይስጡሰርዝ
  2. በኤፍ ኤም 102。1 ከመሐዛ ጋር የምታደርጉት ጭውውት በጣም ተመችቶኛል ብዙ ነገሮችንም ተምሬበታለው በተለይ ስለ በዓሉ ግርማ የጻፍከውን መጽሐፍ የመጽሐፉን ይዘትና የተሰጡትን ኣስተያየቶች ስትናገር በመስማቴ በጣም ደስ ብሎኛል ኣንድ ቀን መጽሐፉን እንደማነብ ተስፋ እያደረኲ ለአንተና ለስራዎች እጅግ ከበሬታ አለኝ::ከምስጋና ጋር

    ምላሽ ይስጡሰርዝ
  3. እንዳለጌታ እንዴት ከርመህልኛል?
    ከማዚ ጋር ያደረከውን ጫወታ ስራ ላይ ሆኜ ተከታተልኩት በጣም ደስ ይላል ።
    ጥሩ ጨዋታ አዋቂ ነህ

    ምላሽ ይስጡሰርዝ
  4. እንዳለጌታ በመጀመሪያ ያገሬ የኢትዮጵያ ልጅ በመሆንህ ኮራሁ፡፡ ሁሉ ጊዜ የአንተ ስራዎች ሳነብ አንተ ቡዙ መፅሀፎች የገነቡህ የእውቀት ጥርቅም መሆንህ አስተውላለሁ ግን ሁል ጊዜ የማስበው ልጠይቅህ የጉራጌ ማህበረሰብ ካፈራቸው ምሁራኖች አንዱ ነህና በጉራጌ ብሄረሰብ ዙሪያ የፃፍካቸው መፅሀፎች በቂ አይደሉም ብዬ አስባለሁና እባክህን የጉራጌ ባህል፣ ማንነት ላይ ተጨማሪ ነገሮች ትፅፋለህ ብዬ ተስፋ ላድርግ አይደል አመሰግናለሁ እድሜና ጤና ተመኘሁ

    ምላሽ ይስጡሰርዝ