2013 ኦገስት 28, ረቡዕ

ያልተቀበልናቸው…(ክፍል 1)


ያልተቀበልናቸው…(ክፍል 1)

…ኢትዮጵያ ውስጥ እያሉ፤ ኢትዮጵያዊ እየሆኑ፤ እንደውጭ ዜጋ የምንቆጥራቸው አሉ፤ እንደ ውጭ ዜጋ ባንቆጥራቸውም ‹የእኛ ናቸው› ብለን አምነን ለመቀበል የምንቸገርባቸው አሉ - ከእነዚህ ብሄሮች ወይም ማህበረሰቦች ጋር አንድ ማዕድ አንቀርብም፤ ከብቶቻቸው ከከብቶቻችን ጋር አይውሉም፤ በጋብቻ ተዛምደን አጥንታቸው ከአጥንታችን ደማቸው ከደማችን ጋር አይዋሃድም፤ አልተቀበልናቸውም -ልክ እንደ መጻተኛ - ልክ እንደ ባይተዋር - ልክ እንደ ድንገተኛ እንግዳ - የሚታዩ ሆነዋል፡፡ ሀገሪቷ ከህጋዊ ባሏ ያልወለደቻቸው ይመስል ሳቅና ለቅሶዋን ከተቀሩት ልጆቿ እኩል የማይካፈሉ የሚመስለን፤ ውለታ የማያኖሩላትና ብድር የማይከፍሉላት የሚመስለን፡፡ ሳናውቃቸው፣ ሳንቀርባቸው፣ ሳንጠይቃቸው የሚያልፍ - ጥላ መስለው፣ ጥላ ለብሰው፡፡

በተለያየ ጊዜ የጻፍኳቸው አንዳንድ የፈጠራ ስራዎቼ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ፤ እነዚህን - የተገፉና የተረሱ የመሰሉኝን ማህበረሰቦችን የሚዳስሱ ሆነው አግኝቼያቸዋለሁ፤ እነዚህ ማህበረሰቦች ብዙዎቹ ሀበሾች አይደሉም፤ ለሀበሾች የሚሰጠውን የክብርና የጌትነት ሹመት የታደሉ አይደሉም፤ በገዛ ቤታቸው እንግዶች ናቸው፤ በገዛ አገራቸው እንደ ቀላዋጭ የተቆጠሩ ናቸው፤ እንዲህ አይነቱ አካሄድ ሊበቃ ይገባዋል ባዮችና የ‹ያ ትውልድ› አባላት ‹‹የኢትዮጵያ ብሄራዊ ስሜት÷ በአብላጫው ከሀበሻ ህዝብ ጋር ነበር የሚዛመደው፡፡ ሀበሻነት ደግሞ ከትግርኛና አማርኛ ቋንቋ ተናጋሪዎች በመለስ የተቀረውን የኢትዮጵያን ሕዝብ አያካትትም›› ብለው ነው የብሄር ጥያቄ እንዲነሳ ያደረጉት፡፡
ጥያቄው የተነሳበትን 50ኛ ዓመት (የወርቅ ኢዮቤል በዓል) እናከብር እንደሆን ነው እንጂ፤ ያለፉት መንግስታት ለጥያቄው መልስ የሚመስል መልስ ሰጡ ወይም ለመስጠት ሞከሩ እንጂ፤ የጠያቂዎቹ ልቦና በመፍትሄ እንዲረካ አላደረጉም፡፡ እንዲህ አብራራዋለሁ፡፡
‹አናሳ› ኢትዮጵያውያን የሚባሉ ነበሩ (?) ቃሉ ደስ አይልም፤ ‹አናሳ› መባል ደስ አይልም፤ አናሳ ማለት ራስንም ያሳንሳል - ተናጋሪውን፡፡ አናሳነት ትንሽነት ነው፤ ትንሽነት ዓይነ-ገብ አለመሆን ነው፤ ቃሉን በስፋት የተጠቀመበት ደግሞ ኢህአዴግ ነው፤ ከኢህአዴግ በፊት አናሳ ብሄሮች ሲል የሰማሁትም ሆነ ያነበብኩለት ኢትዮጵያዊ መንግስት የለም፤ ቃሉን ይጠቀም የነበረው የቁጥራቸውን ማነስ ለመግለጽ ነበር ብዬ እገምታለሁ፡፡
የሆነው ሆኖ አናሳ መባል የሚያሳምማቸው በዝተው ነው መሰለኝ -በየጠረፉ፣ በየጥጋጥጉ፣ በየጉራንጉሩ ያሉ ‹ዝነኛ› ያልሆኑ ብሄሮች - አናሣ አንባል ብለው መንግስትም ሚዲያውም ቃሉን አይጠቀምበት ጀምሯል፡፡
በአደባባይ አንናገረው እንጂ ሁላችንም ጭንቅላት ውስጥ አናሳ የምንላቸው አሉ፤ አናሳ ስል በህሊናችን ውስጥ ቦታ ያልሰጠናቸውና የሚገባቸውን ሥፍራ ያልለቀቅንላቸውን ማለቴ እንጂ ቀጥዬ የምጠቅሳቸውን ጐሣዎችና ማህበረሰቦችን ዋጋ ለመንፈግ የምጠቀምበት አይደለም፡፡
እንደምታውቁት ኢትዮጵያ ውስጥ በትክክል ካልተነገሩን መረጃዎች መካከል አንዱ የብሄር ብሄረሰቦቻችን ቁጥር ነው፤ ‹ከ80 በላይ› ወይም ‹የበርካታ ብሄረሰቦች ሀገር የሆነችዋ ኢትዮጵያ…› ነው የሚሉት ሹማምንቱ፣ ግና ከ80 ወይም ከ85 በላይ ማለት ምንድነው? ማነው እርግጠኛ የሆነውን ቁጥር ሊነግረን የሚገባው?
ከጥቂት ዓመታት በፊት ወደ ደቡብ ኦሞ ሄጄ ነበር- ጂንካ፡፡ ጂንካ ከተማ ውስጥ አንድ ‹ታፔላ› ተሰቅሏል፤ ‹ታፔላ›ው በደቡብ ኦሞ ስር ያሉ ብሄሮችን ስም ይዘረዝራል፤ አስራ ሁለት ናቸው፤ ሀመርን ጨምሮ! ይህንን መረጃ ይዤ፤ እምፈልገውን መረጃ ለማግኘት ስሄድ ግን፤ የጂንካ ባህልና ቱሪዝም አንድ ‹ኤክስፐርት› ብሄሮቹ አስራ ስድስት መሆናቸውን  ነገረኝ -‹‹ታፔላው ከተሰቀለ በኋላ ነው አራቱ ብሄሮች የተገኙት?›› ብዬ ጠየቅኩ፤ ‹‹አዎን! …ወደፊትም ይገኝ ይሆናል!›› ነበር ምላሹ፡፡
በቅርቡ ለሕትመት የበቃው የአንዱዓለም አባተ (የዐፀደ ልጅ) ‹መኤኒት› ልቦለድ ላይም ያስደመመኝ ነገር አግኝቻለሁ፤ ልቦለዱ ለዘመናት የተገፉ፣ የተረሱና የአናሳነት ‹ማዕረግ› የተሰጣቸውን የ‹መኤኒት› ብሄረሰቦችን የሚያሳይ ነው- ፍቅረማርቆስ ደስታ ‹ከቡስካ በስተጀርባ› ብሎ ሀመሮችን እንዳሳየን፣ ዳንኤል ግዛው ጽፎት መዝሙር ፈንቴ የተረጐመው ‹አፍሪካዊው ልዑል› ደግሞ መንጃ፣ በና፣ ኩሌዎችንም እንዳስነበበን፣ ለማ ፈይሣ ‹ጉራጌው›፣ ዳኜ አሰፋ ‹ኬርታ› ብሎ የጉራጌዎችን ማኅበራዊ አኗኗር እንዳመለከቱን… መሆኑ ነው፡፡
‹መኤኒት› ውስጥ አንዲት ቀበሌ አለች፤ ቀበሌዋ ያርጣ ትባላለች፤ ‹በሁለት ሺህ ዓ.ም ነው የተገኘችው፤ ከዚያ በፊት በዚያ አካባቢ ሰው መኖሩ አይታወቅም ነበር› ይላል ልቦለዱ ‹…ምንም አይነት የትራንስፖርትና የመገናኛ አውታር የለም፡፡ አሁን እንኳን በእግር ሃያ ሶስት ሰዓት ተጉዞ ነው እዚያ የሚደረሰው፡፡ በርካታ ጉብታና ሸለቆ ማለፍ፣ እልም ያለ በረሃን ማቋረጥ ያስፈልጋል› (ገፅ 109)
ነገሩ በቸልታ የሚታለፍ መረጃ አይደለም፤ እውነት ከሆነ ከመገረምም አልፎ ያስደነግጣል ‹ያርጣ› ቀበሌ ከመገኘቷ በፊት ማን ነበር አስተዳዳሪዋ? መንግስት እንዴት እንደማዕድንና እንደ ነዳጅ ድንገት አንድ ቀቀበሌ አግኝቻለሁ ይላል? የት ነበሩ? ከከተማው ሃያ ሶስት ሰዓታት በእግር ተጉዞ የሚደረስባቸው እነዚህ ማኅበረሰቦች በትክክል ‹መኤኒት› ናቸው? አኗኗራቸው የእነዚህን የመሰለ ነው ወይስ ራሳቸውን የቻሉ የአንድ ብሄር አባላት? ብሄር ከሆኑ ስማቸው ማን ነው? ተቆጥረዋል ወይ? - የሚል ጥያቄ መጥቶብኛል ልቦለዱን ሳነብ፡፡
አብዛኛው ብሄር የሚንቀውና የሚርቀው ሌላ ‹ብሄር› አለው፤ ሌላ ማኅበረሰብ አለው፤ እነዚህ ‹መገለልና አድልዎ!› የሚደርስባቸውና እንደ አናሳ የሚቆጠሩ ሕዝቦች - ከተለመደው የአኗኗር ፈሊጥ ወጣ ያሉና ያፈነገጡ በመሆናቸው ተከባሪ አይደሉም፡፡
ከዚህ በፊት ‹ኬርሻዶ› በሚለው ኢ-ልቦለድ መጽሐፌ ላይ እንደገለጽኩት፤ ሰባት ቤት ጉራጌ ብትሄዱ ፉጋዎችን ታገኛላችሁ፤ ‹ፉጋዎች በአካባቢው ተወላጆች ዘንድ የተናቁ ናቸው ይባላል፡፡ ቡና እንዲጠጡ ሲጋበዙ እንኳን የራሳቸውን ስኒ ነው ይዘው የሚመጡት፡፡ ስኒያቸው ከሌሎች ስኒዎች ጋር አይደባለቅም፡፡ እነሱ በጠጡበት ስኒ ቡና የሚጠጣ የለም፡፡ እነሱ ቡና ካፈሉ የሚጋብዙትም ሆነ የሚጋበዝላቸው የለም፡፡ ‹ደርግ ነው ከሰው እኩል ያደረገን› ይላሉ፡፡ እኩል ነን ብለው ግን አያምኑም ደርግ መጥቶ፣ አብዮት ፈንድቶ የማያውቁትን ዓለም አሳያቸው ‹ከማንም አታንሱም ከማንም አትበልጡም› አለና፤ ከጓሮ አውጥቶ እደጅ አስቀምጦ አስደነገጣቸው፤ ድንጋጤው አሁንም ቢሆን አልፎ አልፎ በልጆቻቸውና በልጅ ልጆቻቸው ላይ ተባዝቶ አየዋለሁ…›
ስማቸው ‹ፉጋ› አይሁን እንጂ እንደነዚህ ዓይነት ማኅበረሰቦች በየገጠሩ፣ በየብሄሩ አሉ፡፡ - ደርግ ጭቁን ብሄረሰቦች ነበር የሚላቸው፤ እኔ እንደሚገባኝ - ያነበብኳቸው መጽሐፍትም እንደሚጠቁመኝ ደርግ - ኢትዮጵያ የሀበሾች ብቻ እንዳልሆነች ለማመንና ለማሳመን ራሱን አዘጋጅቶ ወታደራዊ ሀይል ተጠቅሞም ነበር፤ ስማቸው ተሰምቶ የማይታወቁ ብሄረሰቦች የት መጣነታቸው እንዲታወቅና የጋብቻና የፍርድ አሰጣጥ ሂደታቸው ምን እንደሚመስል ይዘገብበት ዘንድ በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ የባህል ዓምድ ከፍቶ ነበር፤ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የፎክሎር ትምህርት እንዲሰጥና እያንዳንዱ ባህል ማንነቱ እንዲጠና፣ ትውፊታዊ በዐሉ እንዲመረመር የእውቀት ገበታ አዘርግቶ ነበር፡፡ መስከረም ሁለት ሲመጣ ‹ለዚህ ያበቃን አብዮቱ ነው› ለማለት አለቆቻቸው ፊት የምርቶቻቸውን ውጤት ይዘው፤ በባህላዊ አልባሶቻቸው አጊጠው በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው የምስጋና መብዓ ያቀርቡ ነበር፤ ያም ሆኖ ‹ምሉዕ› አልነበረም - በአፄ ኃይለሥላሴ ዘመን ከነበረው የተሻለ ትኩረት ተሰጣቸው እንጂ!

2 አስተያየቶች:

  1. እውነትም እየታወቀ የተረሳ ነገር ይመስለኛል አንድ ሰው ሀገሬ ብሎ እየኖረ ሀገርን የሚያስተዳድረው ደግሞ አላውቅህም እስካሁን አላገኘሁህም ገና እየፈለግሁህ ነው ሲለው ምን ይሰማው ይሆን በጣም ይከብዳል፡፡ ሃገርን ከሚያስተዳድረው በፊት ሃገር አቅንቶ እሱ አለመታወቁ ይደንቃል በግምት 80 ወይም 85 እያልን ከምንለጥፍ ቁርጡ ይታወቅ፡፡ ይጠና እንዳለም በርታና እስኪ ወገኖቻችን ስንት እንደሆኑ አሳውቀን፡፡

    ምላሽ ይስጡሰርዝ
  2. ጽሁፉ ጥሩ ነው። ነገርግን ፖለቲካዊ ሽውርርና ይየታይበታል። ጽሁፍህ አንድ እውነትን ከመቀበል በጥግ በኩል ተሸዋሮ ማለፍ ፈለገ። ይህ ደግሞ ሊሆን የሚችለው «ውርጅብኙን» አልችለውም፣ የሚያጨበጭቡልኝን አጣለሁ ከሚል ይመስላል። ራስክን የምታምንበትን ሁን።

    ምላሽ ይስጡሰርዝ