2013 ኦገስት 27, ማክሰኞ

ሲጨልምወደ ሰባዎቹ የሚጠጉ የሚመስሉ አንድ አረጋዊ “ልጄ” አሉት አስተናጋጁን፡፡ “የወሰድኩትን መድኃኒት ይዤብህ መጣሁ፣ እባክህን የሰጠኸኝን ወስደህ . . .”
አላስጨርሳቸውም፡፡ ግርግዳው ላይ ወደተለጠፈው ጽሑፍ አመለከታቸው፡፡ ‘የተሸጠ መድኃኒት አይመለስም አረጋዊው’ በለሰለሱ ቃላት መማፀን ያዙ፡፡
“ሰውዬ ዞር በል! ስራ ልስራበት! ለእንቶ ፈንቶ ጉዳይ የማባክነው ጊዜ የለኝም. . .” አለ ቁጣው እየተወለደ፡፡
“ዛሬ በዚህ ሰውዬ እንድጨቀጨቅ ተፈርዶብኛል ልበል?”
“እባክህን ልጄ አሳፋሪ ነገር ደርሶብኝ ነው ዘመድና ዕድር የለለኝ በመሆኑ እንጂ . . . ” አሉ ትሁት በሆነች ፈገግታ ሊያባብሉት እየሞከሩ፡፡
“ቅናሽ ዋጋ ብትከፍለኝም . . .”
“ይሄ ሰውዬ ነካ ያረገዋል ልበል?” አለና ሌሎች መድኃኒት ገዥዎችን ያስተናግድ ገባ፡፡ “ከያዙ አይለቁ” 


“ድህነት ቢፈትነኝ ነው ልጄ” አለ¸ያደፈና የነተበ ነጠላቸውን እያሳዩት፡፡ ነጠላው ከሰውነታቸው በከፋ ሁኔታ ያረጀውን ኮታቸውን ደብቆላቸዋል፡፡
“አቅሜ የደከመ ባይሆን ኖሮ . . . ” ጫማ ካገኘ የከረመ እግራቸውን እያዩ፡፡ አንዲት ተስተናጋጅ “አልመልስም ካለ አልመልስም ነው፡፡ ለምንድነው የሚነዘንዙት?” አለች በሚነጫነጭ ድምጽ “ይሄኮ ፋርማሲ እንጂ አዛውንቶች የሚጦሩበት የድኩማን መርጃ ድርጅት አይደለም”
አነጋገሯን ያልወደደው የሚመስል ሌላኛው ጎልማሳ ደግሞ “መድኃኒቱን ሙሉ በሙሉ የገዙት ከዚሁ መደብር ነው?” የሚል ጥያቄ አመጣ፡፡
“አዎ ዶክተሩ ፅፎ በሰጠኝ መሠረት”
“ምን ያሕል ፈጀብዎት?”
“ሰባ ሁለት ብር ከሰማኒያ አምስት ሳንቲም፡፡ መድኃኒቱን ወስደው ግማሹን እንኳን ቢሰጡኝ ምን አለበት?” አሉ በሃዘኔታ፤ “የሁለታችንንም የጋብቻ ቀለበት አስይዤ ነው ከማምነው ሰው የተበደርኩት”
“መድኃኒቱን ለምን መመለስ ፈለጉ?” ዘንቢል ያንጠለጠሉ ያንዲት ምስኪን እናት ጥያቄ፡፡
በዚህ ጊዜ አስተናጋጁ ጣልቃ ገባ፡፡ “ባህላዊ ሕክምና ብትከታተል ኪስ እንደማታራቁት ገብቷቸው ይሆናላ! ወይ ፀበል ሊያጠምቋት! ወይ . . .”
“ኧይ ልጄ! ጉዳዩን ብታውቀው ኖሮ ያፌዝክበት ምላስህን ታፍርበት ነበር . . .” አሉ እንባ እየተናነቃቸው፡፡
“መድኃኒቱን ምን ላድርገው? ልዋጠው ወይስ ሽንት ቤት ልጨምረው?”
“ለባለቤቴ ነው የምገዛላት ብለው አልነበር? በጠና ታማብኛለች የእድሜዬ ጀምበር እየጠለቀ ባበት ሰዓት ለእህል ያላነሱና ለትምህርት ያልደረሱ ሦስት ልጆች በትናብኝ እንዳትሄድ ፀልይልኝ ብለውኝ አልነበር?”
“ማለቱንስ ብዬህ ነበር ልጄ! . . . ብዬ ነበር”
“እና ሩብ ሰዓት ያህል እንኳን ሳይቆዩ ሃሳብዎን አስሰርዞ የገዙትን መድኃኒት የሚያስመልስ ምን ተአምር ተፈጠረ?! ቅድም የማይመለከተኝን ነገር ሲዘላብዱልኝ ነበር እኮ” አረጋዊው አንገታቸውን ደፉ፡፡ “እኮ ምን ቢፈጠር ነው . . . ?”
“ቤቴ ሳልደርስ ነው አንተ ዘንድ የመጣሁት”
“ለምን?” የሌሎቹ ጥያቄ፡፡
“ሰፈርተኞቼ ደጄ ላይ ሲጯጯሁ አየሁ፡፡ ባቤቴን በህይወቷ ልደርስላት አልቻልኩም!” አሉ አረጋዊው ድምጻቸው እየሻከረ፡፡ እንባቸው እየወረደ፡፡ በመድኃኒት ሻጩ ፊት ላይ ፀፀት ድንጋጤ እየታየ ድፍን መቶ ብር አውጥቶ በሻካራ እጆቻቸው ላይ አኖረው፡፡ ሌሎቹም ኪሶቻቸውን ይፈታትሹ ጀምር፡፡
“ይባርካችሁ ልጆቼ! ከፈን መግዣ ስላልነበረኝ እንጂ . . . ” አንባ ተናነቃቸው፡፡
መንሰቅሰቃቸውን እየቀጠሉ ወጡ፡፡
ፀጥታ!

3 አስተያየቶች: