2013 ኦገስት 24, ቅዳሜ

ስድብ አዘዋዋሪ ጽ/ቤት…



ስድብ አዘዋዋሪ ጽ/ቤት…

…ሰውየው ‹ያልተገባ ስድብ ተሰደብኩ!› ብሎ ተሳዳቢውን ሽማግሌ ፊት አቆመው አሉ፤ ሽማግሌውም የከሳሽና የተከሳሽን ‹ሙሉ ቃል› ካዳመጡ በኋላ፤ ተከሳሹን ይገስፁት ገቡ፤ ተከሳሽም ‹ስድቡ ከአንደበቴ በወጣ ጊዜ ጌሾና ብቅል አብረውኝ ነበሩ፤ ስካር ባይፀናወተኝ ኖሮ ከሳሼ ላይ ተዘባብቼ አንገቴን በሃፍረት ደፍቼ እፊትዎ አልቆምም ነበር!› የሚል ምላሽ ሰጠ፤ ከተሳዳቢው አንደበት የወጡት ስድቦች ተሰዳቢውን ከመግለጽ ይልቅ የሰዳቢውን ደረጃ እና ትክክለኛ ውስጣዊ መልክ የሚያሳይ መሆኑን ሽማግሌው ልብ አሉ! እናም ሁለቱን አስታርቀውና ፍርድ አደላድለው ከሰዳቢና ተሳዳቢ መሃል ሆነው መንገድ ሲቀጥሉ ያያቸው አንድ ሰው ‹አባቴ ከየት ነው?› ብሎ ጠየቃቸው፤ እሳቸውም ‹ስድብ አዘዋውሬ መጣሁ!› አሉ- አሉ ነው እንግዲህ!
…አሁን ባለንበት ዘመን ብዙ ስድቦች አሉ- አለቦታቸው የተነገሩ፤ አለመልካቸው የተገለፁ፤ አለውክልናቸው የተሰጡ፡፡ እነዚህ ስድቦች አንዳንዶቹ የት መጣነታቸው ይታወቃል፤ የፈለቁበት ምንጭ ይገመታል፡፡
ስድብ ከንቀት ማህፀን ብቻ አይደለም የሚወለደው፤ ስድብ ፍራቻ እና ጥላቻም አምጠው ይወልዱታል፡፡ የናቅነውንና በአካልም በመንፈስም እንዳይጠጋን የምንሸሸውን ብቻ አይደለም የምንሰድበው፤ ነገ ከነገ ወዲያ ጉዳት ያደርስብን ይሆናል፣ በእኔ ላይ የማዘዝ ስልጣን ይጐናፀፍ ይሆናል ብለን በስጋት የምንጠነቀቀውንም እንሰድበዋለን፡፡
በስድባችን አንገቱን እናስደፋዋለን፤ በስድባችን መጠጊያ ጥግ እናሳጣዋለን፤ በስድባችን ማረፊያ ጥላውን እናጥርበታለን፡፡
እንደሚታወቀው ተሳዳቢዎች ትናንሽ የምንላቸው ሰዎች ብቻ አይደሉም፤ ከፍተኛ ሹማምንትም ከአንደበታቸው ለሚወጡ ቃላት የሚጠነቀቁ አይመስልም፤ መሪዎችም አንዳንዴ በተሰዳቢዎች መንገድ አካሄዳቸውን እያሳመሩ ፀያፍ ቃላት ‹በሆነ አካል› ላይ ይሰነዝራሉ፡፡
እነዚህ እነዚህ በሆነ ዘመን ህዝብ ባይፋረዳቸው ታሪክ ጣቱን ቀስሮ የክስ ፋይል ያስከፍትባቸዋል፤ ተሰዳቢው ወገን ‹ስድብ ሳይዘዋወርለት› ሰዳቢው ሀገሩን ለቅቆ ቢጠፋ ወይም ከዚህ ዓለም ጠዋት ቢሰናበት የሆነ ቀን÷ በሆነ ቦታ÷ ታሪክ ዘጋቢዎች በማስታወሻቸው ላይ አስፍረው ያሳፍሩት፣ አንገት ያስደፉት ይሆናል፤ ወይም እነሱ ራሳቸው ‹ሂሣቸው›ን ውጠው ይቅርታ ይጠይቁት ይሆናል….
እኔን የሚያሳስበኝ በተናጠል ስለሚሰደቡ ስድቦች አይደለም፤ እኔን የሚያሳስበኝ በጅምላ ስለሚናቅ፣ በጅምላ ስለሚዘለፍ፣ በጅምላ ስለሚሰደብ ሕዝብና ማህበረሰብ ነው፤ ብዙውን ጊዜ ስድቦቹን ማን ፈብርኮ ወደ ህዝቡ ህሊና እንደሚልካቸው አይታወቅም፤ የስድቦቹ ዓላማ የተሰዳቢውን አካሄድ ማሰናከል ነው፤ በመንገዱ እሾህ ለመዝራት፤ በልቦናው ውስጥ ያለችን የተስፋ ጭላንጭል ለማዳፈን…

ብዙ ተረቦች አሉን፤ ብዙ ቀልዶች አሉን፤ ብዙ አባባሎች አሉን፤ እነዚህ ፈጣሪያቸው የማይታወቁ፤ የአንድን ብሔር ስም ጠቅሰው ‹ወደ ሚመለከተው ክፍል የተላኩ› ስድቦች ጐጂ ለመሆናቸው አያጠያይቅም፤ የአንድን ሰው ማንነት ከወጣበት ብሄር ጋር በማያያዝ መስፈሪያ ቁናቸውን የሚያበጁ ‹ህዝቦች› አሉ፤ እነዚህን ህዝቦች በፍርድ አደባባይ አቁሞ የሚከሳቸው የለም፡፡
አንዳንዱ የዚህ ትውልድ አባል- (ከአባቶቻችን ሲወርድ ሲወራረድ በመጣው መሰረት ልበል?) የስድብ ሃብታም ነው፤ የሚተርበው ብሔር አያጣም፤ ሌላውን አሳንሶ አስጐንብሶ ካላሳየ እሱ ቀና ቢል እንኳን የሚታይ አይመስለውም፤ ልቡ በነቀፌታ የተሞላ ነው፤ አንዳች የስድብ መንፈስ-በየቤቱ- በየቤተመንግስቱ- በየቤተ ክርስትናውና በየቤተ እስልምናው ሰፍኗል፤ የሆነውን ብሔር ለይቶ፣ የሆነውን ወገን አግልሎ፤ ‹እኛ ካልተሳተፍንበት የልማት እስክስታው አይሰምርም፤ እኛ ካልደሰኮርንለት አምላክ ቸርነቱን አያዘንብም› ማለት የተለመደ እየሆነ ነው!
በየጥጉ አዲስ የስድብ ዓይነት ተፈብርኳል፤ እያንዳንዳችን በየልባችን፣ በየቤታችን፣ በየብሔራችን አንድ የምንጠላው ብሔር ተሰናድቶ ተሰጥቶናል፡፡ ያለፈውን ስርዓት ከመቃወምና ‹…ለእድገታችሁ ማነቆ የሆነው ስርዓቱ ነው› ከማለት ይልቅ፤ የአንድ ብሔር ስም ተነግሮን ‹እነሱ ባይኖሩ ኖሮ የትና የት በደረሳችሁ› እንባላለን፤ ደግሞ ‹ተመልሰው እንዳይመጡ እኛና እናንተ እጅና ጓንት ሆነን እንስራ› እንባላለን፡፡ እስኪ ወደ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት መጸዳጃ ቤቶች ሂዱ-ሂዱና በግድግዳዎቹ ላይ የተፃፉትን አንብቡ፤ ብዙዎቹ ብሔር ተኮር ስድቦች ናቸው፤ የስድቦቹ ምንጮች በአብዛኛው ‹ካድሬዎች› ናቸው፤ እነዚህ ካድሬ የሆኑና ያልሆኑ፣ በተቃዋሚነትና በደጋፊነት ጐራ የተሰለፉ ተሳዳቢዎች መጽሐፍ ሲጽፉም፤ በታሪክና በባህል ላይ ያተኮረ ጥናት ሲያቀርቡም እነዚያ ስድቦቻቸውን ያርከፈክፉባቸዋል፡፡
…ስድብ ማዘዋወር ያስፈልጋል፤ ስድብ ለማዘዋወር ደግሞ የፍርድ አደባባይ ግድ አይደለም፤ ጊዜ ነው መድሃኒቱ! አይተናል- ጊዜ ያነሳው ቅል ድንጋይ ሲሰብር አይተናል! እንዲሰበር የማይፈልግ ‹ንቡርና ንዑድ› ድንጋይ ቅል ነው ብሎ፤ ባዶ ጭንቅላት ነው ብሎ፤ መራራ ነው ብሎ ቅሉን ሊንቀው አይገባም፤ ይህ ‹እኛ ድንጋይ ነን፤ ሌሎች ግን ቅሎች› ብሎ ሌላውን ንቆና አርቆ የመመልከት አባዜ ከላይ ብቻ ሳይሆን ከታችም አለ፤ ታች ያለው ማኅበረሰብም የወረወሩለትን ስድብ ነው ዘሎ የሚያቅፈው፤ ‹አይመለከተኝም፤ አይመጥነኝም› ብሎ ወደመጣበት የመመለስ ልምድም እውቀቱም ያለው አይመስልም፡፡
…ከመሰዳደብ፤ ነቀፌታ በተሞላበት ሁኔታ ከመተቻቸት፤ ‹ድሮስ ከእንትን ማህበረሰብ ተወልደህ ካንተ ምን ይጠበቃል?› ከመባባል፤ ቁጭ ብሎ መነጋገር ነው የሚሻል! ልሂቃኑ እንደሚሉት አፄ ኃይለሥላሴ ኤርትራን ላለማጣት የወሰዱት እርምጃ ማባበል ነው- ተወላጁን እሽሩሩ ብሎ ማስተኛት፤ የለቅሶ ድምፅ ባሰማ ቁጥር የሹመት ጡጦ ባፉ ማጉረስ፤ የነፃ ትምህርት እድል እንዲያገኝ የአውሮፓውያንን ውሃ ማጠጣት… በየነገሩ የተከበረ ወንበር እንዲለቀቅላቸው ማድረግ፤ ይኼ ነበር የአፄው ብልሃት! ሆኖም መፍትሄ አላመጣም፤ የነፃነቱ ጥያቄ አላባራም፤ የአማፂው ቁጣ አልበረደም፤ እየተባባሰ ሄደ እንጂ! ጓድ መንግስቱ ኃይለማርያም ደግሞ በአንድነት ስም አስገድዶ፣ አንበርክኮ፣ ተወላጁን ጠልቶና ተጠራጥሮ የስልጣን ዘመኑን ከእነሱ ጋር ሲዋጋ እና ሲያዋጋ አሳለፈው፤ ሆኖም ኤርትራውያን አልተንበረከኩም - ይጋፈጡ ይጋደሉ ያዙ እንጂ!
‹መፍትሄዎቹ ልክ አልነበሩም› ይላሉ የፖለቲካ ተንታኞቹ፤ ‹ማባበልም ማስገደድም መፍትሄ አይሆኑም፤ አልሆኑም፣ አኩራፊውን ወገን ቁጭ አድርጐ እስኪ እንነጋገር በውስጥህ ያለውን ህመም አውጣው፤ ፤ በምን አስቀየምኩህ፤ ምን አጐደልኩብህ እስኪ ወንድሜ እንነጋገር ማለት ነበር መፍትሄው! ለዚያም ነው ቁጣው በርትቶ፣ አመጻው ተደራጅቶ የኋላ ኋላ የራሳቸውን እድል በራሳቸው የወሰኑት- የተገነጠሉት፡፡
ለመጪው ትውልድ ‹በደም› የሚመለስ የቤት ስራ እየተውን ያለ ይመስለኛል፤ የመጪው ትውልድ አባላት እኛ በመጣንበትም ሆነ አባቶቻችን በተመላለሱበት የመሰዳደብ መንገድ ባይሄድ እንመርጣለን፤ እኛ ፈትለንና ገምደን ያቆየነው፣ አለባብስን ያረስነው ነገር ነገ ከነገ ወዲያ ‹… ያልተዘጋ ፋይል አለ!› ብለው በጥይት ቋንቋ እንዲነጋገሩ መፍቀድ የለብንም- ሰርተን በቆየንላቸው መንገድ ደም እንዳያጐርፍበት፤ ሰርተን ባቆየንላቸው ተቋማት ስድብ እንዳይፈበረኩበት ጥንቃቄ ማድረግ ያሻል፡፡
…ባለፉት ሁለት ሶስት አመታት ብቻ፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ወደ ተለያዩ ክልሎች የመሄድ እድል ገጥሞኝ ነበር- የሄድኩባቸው ምክንያቶችና የተጓዥ ቡድኑ ስብጥር የተለያየ ነው፡፡ የጐበኘኋቸው የገጠር መንደሮችና ከተሞች (ከሶማሌ እስከ መቀሌ፤ ከሐረር እስከ ሐመር፤ ከአዋሳ እስከ አሰላ፤ ከቡታጅራ እስከ እንጅባራ፤ ከአሣይታ እስከ ወላይታ፤…) ተመሳሳዮች ናቸው፤ ጭቁን ተስፈኞች ናቸው፤ እኩል የጐደለባቸው ናቸው፤ እርስ በርስ የሚተዛዘኑ፣ እርስ በርስ የሚተዛዘሉ፤ ሣቅና ለቅሶ የሚበዳደሩ ናቸው፤ የደበበ ሰይፉን ‹ከአክሱም ጫፍ አቁማዳ›ን የሚያስታውሱን! ወደ አዲስ አበባና ወደ አንዳንድ የክልል ከተሞች ስትመጡ ግን፤ አብዛኛው የተማረ የተባለው ክፍል በምትናገሩበት ቋንቋ ይመዝኗችኋል፤ ቋንቋችሁ የብሄራችሁን ማንነት ካልነገራቸው በስማችሁ ይለዩዋችኋል፤ ስማችሁ ብሄራችሁን ካልነገሯቸው እስከ አያቶቻችሁ ድረስ ሊቀጥሉ ይችላሉ- ከዚያ በኋላ ነው መግባባት ወይም መለያየት የምትችሉት፤ ከተማ ውስጥ ከሳሽና ወቃሽ ይበዛል- የእኔን ዳቦ ሰርቆ የጐረሱት የነእንቶኔ ብሄር አባላት ናቸው ማለት ይፈልጋል፤ ከተማ ውስጥ ስድብና ነቀፌታ ይበዛል- የሰርቶ በዩን ጉልበት የሚያልፈሰፍሱ ቃላት በመሰንዘር በአቋራጭ መክበሩን ይችልበታል፡፡
…በአፋር ማህበረሰብ ዘንድ አዲት ሴት መልኳ ባያምር፣ ቁመቷ አለቅጥ ቢያጥር፣ እጇም እግሯም ዓይኗም አመሏም- ሁለ ነገሯ ችግር ቢኖረው እንኳን የሚያገባት አታጣም፤ ለምን ቢባል በማህበረሰቡ ዘንድ ‹…ንቀው ያለፏት ሴት ሌሎችን የሚንቅ ትወልዳለች› የሚል አባባል አላቸውና!
…በአማራ ደግሞ ‹የተናቀ ያስረግዛል›፣ ‹የጠሉት ይወርሳል የፈሩት ይደርሳል› ይባላል- መጽሐፉም ደግሞ ‹ግንበኞች የናቁት ድንጊያ እርሱ የማዕዘን ራስ ይሆናል› ይላል- ‹የናቁሽ ሁሉ ከእግርሽ ጫማ በታች ወድቀው ይሰግዳሉ› ይላል፡፡
ማኅበረሰቡም ሃይማኖቱም እግዜር ለተናቁ፣ ለተበደሉ እና ለተሰደቡ እንደሚያደላ የሚያምኑ ይመስላሉ፡፡ ታሪክም የተናቁና የተሰደቡትን እየመረጠ፣ ከየሜዳው እየለቀመ፣ ከየጫካው እየጠራ፣ ከየጓሮውና ከየምድጃው ስር እየጐተተ ‹ከፍ ያለ ቦታ› ሰጥቷቸዋል፤ ዙፋን አድሏቸዋል….
ደርግን ውሰዱ፤ ደርግ ውስጥ ከ‹ታችኛው› ማኅበረሰብ የመጡ ሰዎች ነበሩበት- አሽከር ተብለው የተገፈተሩ፤ ባርያ ተብለው እንደ መገልገያ ዕቃ የተቆጠሩ፡፡ በአፄው ዘመን ለባርያ ይሰጥ የነበረውን ቦታ ታውቁታላችሁ- ቢወልዱ ልጆቻቸውን እንደራሳቸው መቁጠር አይችሉም፤ የገዢዎቻቸው ንብረት ናቸውና፡፡ መኳንንቱ ሲሞቱ እንኳን ከሚወዷቸው ባርያዎች አንዱ አብሯቸው በህይወት እንዲቀበር ይደረግ ነበር- ‹ባርያው› ይባል የነበረው- ‹ባርያ› ተብሎ ይሰደብ የነበረው መንግስቱ ኃይለማርያም መጣና ተሰዳቢዎቹንም ራሱንም ነፃ አወጣ…
ከወጣ በኋላ ግን እሱ ራሱ ተሳዳቢ ሆነ፤ በከፈቱበት ጦርነት ምክንያት ኤርትራውያንን ጠላ፤ የትግራይ ተወላጆችን በአይነ ቁራኛ መከታተል ያዘ፤ በየንግግሮቹ መሐል ክብረ-ነክ የሆኑ ቃላትን አርከፈከፈ፤ ‹ገንጣይ አስገንጣይ ወንበዴዎችና የእናት ጡት ነካሾች ናቸው› ብሎ ተዋጋቸው፤ ውጊያው በተሰዳቢዎቹ አሸናፊነት ተጠናቀቀ፤ /ተሰዳቢዎቹ ቅስማቸውን የሚሰብር ስድብ ይሰደቡ እንደነበር እንጂ ስድቡን መልሶ ማስታወስ ተገቢ አይመስለኝም/፤ ስልጣን ላይ ወጡ፤ ደርግ እንደ ማተብ በአንገቱ ያሰረውን የአንድንትን ክር በጥሰው መዘባበቻ አደረጉት ያጌጠበትን ባንዲራ ጨርቅ ነው አሉት፤ ስፍር ቁጥር የሌለውን ሰራዊት ‹ከሰዳቢዎቻችን ወገን ነህ!› ብለው አንከራተቱት…
ተሰዳቢ የነበረው ኢህአዴግ ደግሞ ስልጣን ላይ ሲወጣ፤ ‹ነፍጠኛ!› የሚል ስድብ አመጣ ‹…እነዚህ የአማራ ነፍጠኞች….› እያለ!  ሌሎቹ ስድቦቹ ደግሞ ምን ነበሩ?
እኔ እንደሚታየኝ ሶስቱም ተመሳሳይ የሆነ የስድብና የንቀት ‹ክህሎት› አላቸው፤ የተወሰነውን ማህበረሰብ በማንቃትና በማጥላላት፣ የሚደርስባቸው የለም፤ አንዱን ወይም ሁለቱን ብሔር ነጥለው በጅምላ በማውገዝ ረገድ እኩል ውጤት አላቸው፡፡ የሚያዋርዱት፣ የሚንቁት፣ የሚገፈትሩት የሆነ ‹አካል› ከሌለ፤ በህይወት ያሉ አይመስላቸውም፡፡
ይሄ አገሪቱ ያለችበት የትናንትና የዛሬ መልክ ነው-
ከዚህ በፊት ያልኩትን ልድገመውና- ይህቺ ሀገር ታምማለች መታመሟን አልካድንም፤ መንግስትም ህዝብም የማከም አገልግሎት ለመስጠት- አቅሙ በፈቀደው ልክ- እየተረባረበ ነው፤ ግና መቅደም ያለበት እንዳይከተል እሰጋለሁ፤ ቀደም ሲል አየኋቸው ጐበኘኋቸው ያልኳቸው ቦታዎች እንዳይመረዙና ስድብ አርግዘው እንዳይኖሩ እሰጋለሁ፤ በየህሊናቸው ውስጥ የተበዳይነት ስሜት እንዲሰርፅባቸው ካደረግን አንድ ቀን - ያቺ በፍቅር አስተሳስራ ያኖረቻቸው የአክሱም ጫፍ አቁማዳ- ሌባ ይሰርቃታል፤ ብል ይበላታል፡፡
የሌባውም የብሉም ተባበሪ ላለመሆን ደግሞ መፍትሄው ቀላል ነው- በብሔር ስም በየስርጓጐጡ የሚቀለድ ቀልዶችን፣ ተረቶችን፣ አባባሎችን፣ ተረቦችን ላለመስማትና ላለማማት መዘጋጀት ያስፈልጋል፡፡
 …እነዚህ ናቸው-አንጋጠን የምንተፋቸው ምራቆች፤ እነዚህ ናቸው-አንጋጥጠን ተፍተን ተመልሰው መጥተው የገዛ ፊታችንን የሚያስቀይሙት፡፡
አዎን፤ ሁላችንም ስድቦች ወደ መጡበት የሚመልስና ወደሚመለከተው ክፍል የሚያዘዋውር ጽ/ቤት በየህሊናችን ልናቋቁም ይገባል፤ አውቀንም ይሁን ሳናውቅ በብዙዎች ልቦና ላይ የማይታይ ቁስልና ሰንበር እንዲታተም አድርገናልና!

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ